የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን የኤርትራ አቻውን ሁለት ለአንድ በመርታት አምስተኛ ደረጃን ይዞ ውድድሩን ጨርሷል።
የወቅቱ የሴካፋ ውድድር አሸናፊ ዩጋንዳ ጨዋታውን በጥሩ አቀራረብ የቀረበ ይመስላል። ኤርትራዎች ደግሞ ከኳስ ጀርባ በመሆን ሲጫወቱ ታይቷል። ይህ ቢሆንም ግን የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረገችው ኤርትራ ነች። ቡድኑም በ9ኛው ደቂቃ በዓሊ ሱሌማን አማካኝነት ጥሩ ጥቃት ፈፅሟል። ከስምንት ደቂቃዎች በኋላም ሳዶር የማነህ ሌላ ጥቃት በፈጣን የማጥቃት ሽግግር በማድረግ ቡድኑን መሪ ለማድረግ ዳድቶ ነበር።
ዩጋንዳዎች በበኩላቸው ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም እስከ 20ኛው ደቂቃ ድረስ አንድም ሙከራ አልሰነዘሩም። በተጠቀሰው ደቂቃ ግን ስቴቨን ሙክዋላ ፍጥነቱን ተጠቅሞ ተከላካዮችን አምልጦ በመግባት ወደ ግብ የመታው ኳስ ዒላማውን ስቶ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። በፈጣን የማጥቃት እና የመከላከል ሽግግሮች ጨዋታውን የቀጠሉት ኤርትራዎች በ33ኛው ደቂቃም ሌላ ያለቀለት ጥቃት ሰንዝረው ነበር። በዚህም መድሃኔ በጥሩ መናበብ ከዓሊ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ልኮት መክኖበታል።
የመጀመሪያው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ ስድስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በቀኝ መስመር ወደ ኤርትራ የግብ ክልል ያመሩት ዩጋንዳዎች ግብ አስቆጥረው መሪ ሆነዋል። በዚህም ናጂብ ይጋ ከቀኝ መስመር የተሻገረለትን ኳስ በሩቁ ቋሚ ሆኖ በማግኘት ወደ ግብነት ቀይሮታል። በቀሪ የአጋማሹ ደቂቃዎች ኤርትራዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ቢጥሩም ሀሳባቸው ሳይሳካ ቀርቷል።
በሁለተኛው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ማስመልከት የቀጠለው ጨዋታው እስከ 60ኛው ደቂቃ ዐይንን የሚይዝ አልነበረም። በ60ኛው ደቂቃ ግን የኤርትራው አጥቂ ዓሊ ሱሌይማን ከዩጋንዳው ግን ጠባቂ ቻርለስ ሉክዋጎ ጋር በእንቅስቃሴ ተጋጭቶ ጉዳት አስተናግዷል። ሜዳ ላይ ራሱን ስቶ ከሜዳ የወጣው ተጫዋቹም በስታዲየም ወደሚገኘው ጊዜያዊ የህክምና ስፍራ ተወስዷል። ተጫዋቹ በስፍራው በተደረገለት ህክምናም ካጋጠመው ድንገተኛ አደጋ መለስ እንዲል ቢሆንም ለተጨማሪ ህክምና ወደ ጥበበ ጊዮን ሆስፒታል ተወስዷል።
በአንፃራዊነት ወደ ግብ በመድረሱ ረገድ ተሽለው የታዩት መሪዎቹ ዩጋንዳዎች በ66ኛው ደቂቃ ስቴቨን ስርዋዳ አክርሮ በመታው ኳስ ተጨማሪ ጎል ለማግኘት ፍላጎት እንዳላቸው አሳይተዋል። ይህንን አስደንጋጭ ሙከራ ያደረገው ቡድኑም በ72ኛው ደቂቃ ፍላጎቱ ፍሬ አፍርቱ በስቴቨን ሙኩላ ጎል መሪነቱን ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል።
ጨዋታው ከቁጥጥራቸው ውጪ የሆነባቸው ኤርትራዎች ሁለተኛውን ግብ ካስተናገዱ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ በስምኦን ሀብቴ አማካኝነት ምናልባት ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ጥረዋል። ነገርግን ኳሱ መረብ ላይ ሳያርፍ ቀርቷል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ተጠናቆ በጭማሪ ደቂቃ ግን ቡድኑ በዮናታን ተከስተ አማካኝነት የማስተዛዘኛ ጎል አግኝቷል። ጨዋታውም በዩጋንዳ ሁለት ለአንድ አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ዩጋንዳ አምስተኛ ደረጃን ስትይዝ ኤርትራ ደግሞ ስድስተኛ ደረጃን በመያዝ ውድድሩን ቋጭተዋል።