ደቡብ ሱዳን በሴካፋ ውድድር ሦስተኛ ደረጃን ይዛ ፈፅማለች

ሦስተኛ ደረጃን ለመያዝ የተደረገው የደቡብ ሱዳን እና ኬንያ ጨዋታ ደቡብ ሱዳንን አንድ ለምንም አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።

ዝግ ያለ እንቅስቃሴ የታየበት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ደቂቃዎች የጨዋታ ክፍለ ጊዜ የግብ ማግባት ሙከራ ለማስተናገድ አስራ አንድ ደቂቃዎች ወስደውበት ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ኳስ በእጅ በመነካቱ ደቡብ ሱዳን ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት አግኝታ በዶሚኒክ ኮርኔሊዮ አማካኝነት ሞክራ ነበር። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው እየገቡ የመጡት ኬንያዎች በበኩላቸው በሩብ ሰዓት የመጀመሪያ የሰላ ጥቃት ሰንዝረው መሪ ሊሆኑ ነበር። በዚህ ደቂቃም የግራ መስመር ተጫዋቹ ማሎባ ኦሊቨር ተከላካዮችን አምልጦ በመወጣት ግብ ክልል ጋር በመድረስ ከግብ ጠባቂው ጋር አንድ ለአንድ ቢገናኝም ኢማኑኤል አባል ኳሱን በጥሩ ቅልጥፍና አምክኖበታል።

ሲያጠቁም ሆነ ሲከላከሉ በህብረት የሆነው ኬንያዎች በ22ኛው ደቂቃ ንጁጉና ኮሊንስ በሞከረው ኳስ ሌላ ጥቃት ሰንዝረዋል። ከአስር ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ደቡብ ሱዳኖች በቀኝ መስመር በተደራጀ መንገድ ኬንያዎች የግብ ክልል አምርተው እጅግ ወርቃማ ዕድል ፈጥረው ነበር። ነገርግን ዳኒ ጉማኖክ ከአጋሮቹ ጋር ጥሩ ተጫውቶ ወደ ሳጥን የላከው ኳስ መዳረሻው ውጪ ሆኖ አጋጣሚው መክኗል። የመጀመሪያው አጋማሽም ያለ ጎል ተጠናቆ ተጫዋቾች ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

የሁለተኛውን አጋማሽ በተሻለ ተነሳሽነት የቀረቡት ኬንያዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመሄድ ቀዳሚ ለመሆን ሲታትሩ ታይቷል። በዚህም አጋማሹ እንደተጀመረ የቅጣት ምት ያገኘው ቡድኑ አጋጣሚውን ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። ከዚህ በተጨማሪም ማሎባ ኦሊቨር በ60ኛው ደቂቃ ከተከላካዮች ጋር ታግሎ ያገኘውን ኳስ ወደ ግብ ልኮት የነበረ ቢሆንም ኳስ እና መረብ ሳይገናኙ ቀርቷል። ደቡን ሱዳኖች ግን በአንፃራዊነት ወደ ግባቸው በማፈግፈግ ሲጫወቱ ተስተውሏል።

ጨዋታው ቀጥሎም ኬንያ በ74ኛው ደቂቃ ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት አግንታ ነበር። የተገኘውንም የቅጣት ምት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ሙቺሪ ቦኒፌስ ወደ ግብ ልኮት ግብ ጠባቂው ኢማኑኤል አባል አውጥቶታል። ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ደቡብ ሱዳን በተመሳሳይ የቅጣት ምት አግኝታ በዳታ ክሪስቶፈር አማካኝነት ወደ ግብነት ልትቀይረው ነበር። ይህ ሙከራ ወደ ውጪ ቢወጣም በ78ኛው ደቂቃ ቡድኑ በዳኒ ጉማኖክ አማካኝነት ወደ መሪነት የተሸጋገረበትን ጎል አግኝቷል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ግብ አስቆጥረው ወደ ጨዋታው ለመመለስ ያሰቡት ኬንያዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች መፍጨርጨር ይዘዋል። በዚህም በ86ኛው ደቂቃ ኦቴኖ ኦድሂያምቦ ከርቀት በመታው እንዲሁም በ87ኛው ደቂቃ ኦሉች ኦቺንግ ከቅጣት የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ በሞከረው አጋጣሚ የደቡብ ሱዳንን ግብ ፈትሸዋል። ነገርግን ውጥናቸው ሳይሰምር ቀርቷል። ጨዋታውም በደቡብ ሱዳን አንድ ለምንም አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ደቡብ ሱዳን የውድድሩን ሦስተኛ ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ በጨዋታው እጅ የሰጠችው ኬንያ ደግሞ አራተኛ ሆና ውድድሩን ቋጭታለች።