አዲሱ የዐፄዎቹ ተጫዋች በቅርቡ ለተቋቋመው የትውልድ ከተማው ክለብ የትጥቅ ድጋፍ አድርጓል

ቅዱስ ጊዮርጊስን በመልቀቅ ወደ ዐፄዎቹ በቅርቡ ያመራው አብዱልከሪም መሐመድ በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ላይ እየተካፈለ ላለው የትውልድ ከተማው ክለብ የትጥቅ ድጋፍን አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በምድብ ሁለት የተደለደለው ወንዶ ገነት ወረዳ እስከ አሁን ከምድቡ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች ድል ቀንቶታል፡፡ በእግር ኳሱ የተለያዩ ተጫዋቾችን ማፍራት ብትችልም በክለብ ደረጃ እምብዛም ተሳትፎ ያልነበራት ወንዶ ገነት በአሁኑ ሰዓት በአካባቢው ያለውን እግርኳስ ለማንቃት ከፍተኛ እንቅስቃሴ ማድረግን ጀምራለች፡፡

በክልል ክለቦች ሻምፒዮና ውጤታማ አጀማመር ያሳየው እና ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግም ለመግባት ውጥን ያዘለው ክለቡ ከከተማው በወጣው አብዱልከሪም ድጋፍ ተደርጎለታል፡፡ እግር ኳስን ተወልዶ ባደገባት ወንዶ ገነት የጀመረው የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ፣ ሲዳማ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ እንዲሁም የወቅቱ የፋሲል ከነማ ተጫዋች ክለቡ በመቋቋሙ ደስተኛ እንደነበር የተናገረ ሲሆን በዚህም የመጫወቻ ጫማዎች፣ የመጫወቻ መለያ እና ተጨማሪ ትጥቆች፣ የልምምድ ኮኖች እና ሌሎች የስፖርት ማቴሪያሎችን ነው ለቡድኑ ድጋፍ ማድረግ የቻለው።

ተጫዋቹ ለሶከር ኢትዮጵያ እንደገለፀው በቀጣይም ክለቡ ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ እንዲያልፍ የበኩሉን ድርሻ እንደሚወጣ የገለፀ ሲሆን በቀጣይም ከክለቡ ጎን በየትኛውም ወቅት አብሮ እንደሚሆን ተናግሯል።

አብዱልከሪም ከዚህ ቀደም ለተጫዋተበት ደቡብ ፖሊስ ከጌታነህ ከበደ ጋር በጥምረት ተመሳሳይ ድጋፍ ማድረጉ ይታወሳል ፡፡