ሰበታ ከተማ የሦስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል።
ፍፁም ገብረማርያም ውላቸውን ካደሰሱት መካከል ነው፡፡ ከወለጋ ዩኒቨርሲቲ ከተገኘ በኃላ ለሙገር ሲሚንቶ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ ኤሌክትሪክ፣ ወልዲያ፣ መከላከያ እና ያለፉት ሁለት የውድድር ዓመታትን በሰበታ ያሳለፈው አጥቂው በክለቡ አንድ ተጨማሪ ዓመት ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል፡፡
ናትናኤል ጋንቹላም ውሉን በሰበታ አድሷል፡፡ ፋሲል ከነማን ከለቀቀ በኃላ ወደ ሰበታ ከተማ ተመልሶ ከከፍተኛ ሊጉ ጀምሮ ክለቡን እያገለገለ ያለፉትን ሶስት የውድድር ዒመታት ያሳለፈው የመስመር ተጫዋቹ ተጨማሪ አንድ ዓመት በሰበታ ለመቆት ውል አድሷል፡፡
ሌላኛው ውሉን ያራዘመው ዱሬሳ ሹቢሳ ነው፡፡ ከአዳማ ከተማ ወጣት ቡድን የተገኘው እና ዐምና በነገሌ አርሲ አሳልፎ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ሰበታን የተቀላቀለው ተጫዋቹ ከተጠባባቂ ወንበር በመነሳት ወሳኝ ግቦችን ያስቆጠረ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት በሰበታ መቆየቱን በፊርማው አረጋግጧል፡፡