ሲዳማ ቡና በስሩ ላሉት አራት ቡድኖች ትጥቅ ከሚያቀርብ ተቋም ጋር ስምምነት ፈፀመ

ሲዳማ ቡና ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት ጋር የስፖርት ትጥቅ እና የደጋፊዎች ቁሳቁስ ለማግኘት ስምምነት ፈፅሟል።

በ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ራሱን በሜዳ ላይ አጠናክሮ ለመቅረብ እንቅስቃሴ ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና ከሜዳ ውጪ ያሉ ስራዎችንም ጎን ለጎን እያከናወነ ይገኛል። ከእነዚህ ስራዎች አንዱ የሆነው ደግሞ በክለቡ ስሩ የሚገኙትን ቡድኖች በትጥቅ ከሚደግፍ እንዲሁም ለደጋፊዎች ማሊያን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ከሚያቀርብ ተቋም ጋር መስማማት ይገኝበታል።

 በትናንትናው ዕለት በተፈፀመው በዚህ ስምምነት ላይ ሲዳማ እና ጎፈሬን ወክለው አቶ ኤርሚያስ ተስፋዬ እና አቶ ሳሙኤል መኮንን (በቅደም ተከተላቸው) ተገኝተዋል። በስምምነቱ ላይ እንደተገለፀው ከሆነ ጎፈሬ የስፖርት ትጥቅ አምራች ድርጅት በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፈው ዋናው የሲዳማ ቡና ቡድን ውጪ በክለቡ ስር ላሉት አራት ቡድኖች (ከ23 ዓመት በታች፣ ከ20 ዓመት በታች፣ ከ17 ዓመት በታች እና የሴቶች ቡድን) ሦስት አይነት ማሊያዎች ከአሠልጣኝ ቡድን አባላት አልባሳት ጋር ለማቅረብ እንደተስማማ ታውቋል።

ከላይ የተገለፁት አራት ቡድኖችን በስፖንሰር ሺፕ መልክ የመጫወቻ ሦስት አይነት ማሊያዎችን የሚያቀርበው ጎፈሬ የመለማመጃ፣ የመጓጓዣ እና የመመገቢያ አልባሳትንም እንደሚሰጥ ተብራርቷል። ከዚህ በተጨማሪ ክለቡ ለደጋፊዎች የሚሆኑ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ጎፈሬ እንዲያቀርብ ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚህም በተለያዩ ዙሮችን ማሊያ፣ ስካርቭ፣ ፎጣ፣ የመኪና ጌጣጌጦች እና የተለያዩ ቁሳቁሶችን ተቋሙ በሽያጭ መልክ በተመጣጣኝ ዋጋ ለክለቡ እንደሚያስረክብ እና ክለቡ ደግሞ ለደጋፊዎቹ እንደሚሸጥ ተረድተናል። ሁለቱን ጉዳዮች የያዘው ስምምነትም ለሁለት ዓመታት እንደሚዘልቅ ተነግሮናል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጎፈሬ በቅርቡ ለተቋቋመው የኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበርም ለአባላቱ ማሊያዎችን ለማቅረብ ስምምነት እንደፈፀመ የተቋሙ ባለቤት አቶ ሳሙኤል መኮንን ለሶከር ኢትዮጵያ ገልፀዋል። ለአምስት ዓመታት የሚቆየው ስምምነት በዋናነት ማኅበሩ የተለያዩ ሥራዎችን ሲከውን የሚብሰው እንዲሁም ለአባላቱ የሚያቀርበው ልዩ መለያ የማቅረብ እንደሆነ ሰምተናል።

ከኢትዮጵያ እግርኳስ ደጋፊዎች ማኅበር ዜና ጋር በተገናኘ ማኅበሩ በመጪው ማክሰኞ በአዲስ አበባ ስታዲየም የአባላት ምዝገባ እንደሚጀምር ፕሬዝዳንቱ አቶ ምንያህል ነግረውናል።

ያጋሩ