ለሰበታ ከተማ እና ለሀድያ ሆሳዕና የፈረመው አጥቂ መነጋገሪያ ሆኗል

በባህርዳር ከተማ ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እያለው ለሰበታ ከተማ እና ሀድያ ሆሳዕና በቀጣዩ ዓመት ለመጫወት ፊርማውን ያኖረው አጥቂ በብዙሀኑ ዘንድ መነጋገሪያ እየሆነ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች የዝውውር ገበያው ከተከፈተ በኋላ በርካታ ተጫዋቾች ወደ ተለያዩ ክለቦች እያመሩ ይገኛሉ፡፡ ካለፉት ዓመታት አንፃር ዘንድሮ ይበልጥ ከፍተኛ ገንዘብ ለዝውውር እየተሰጠም እንደሚገኝ ሰምተናል፡፡ ምንም እንኳን የተጫዋቾች ዝውውር እርግጠኝነቱ የሚረጋገጠው በክልል ወይንም በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ቢሆንም ተጫዋቾች ግን ለአንድ ክለብ ፈርሞ ከመቀመጥ ይልቅ በተለያዩ ጥቆማጥቅሞች የተነሳ በተደጋጋሚ በክረምቱ የዝውውር ገበያ ፊርማቸውን ለተለያዩ ክለቦች እያኖሩ መነጋገሪያ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡ ልክ የዛሬ ዓመት አስቀድሞ ለወላይታ ድቻ ከፈረመ በኋላ ከወልቂጤ ከተማ ጋርም ተመሳሳይ ስምምነት ፈፅሞ በመጨረሻም ማረፊያውን ባህር ዳር ከተማ አድርጎ የ2013 የውድድር ዓመትን በጣና ሞገዶቹ ቤት ያሳለፈው አጥቂው ባዬ ገዛኸኝ ዘንድሮም አወዛጋቢ የሆነ ድርጊትን ፈፅሟል፡፡

ባለፈው ዓመት ለባህር ዳር ከተማ የሁለት ዓመት ፊርማን ካኖረ በኋላ አንዱን ዓመት በክለቡ ውስጥ ያሳለፈው ባዬ በባህር ዳር በ2014 የሚያቆየው ውል እያለው ለሰበታ ከተማ እና ለሀድያ ሆሳዕና በተመሳሳይ የሁለት አመት ውል መፈረሙን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ በባህር ዳር ከተማ አንድ ቀሪ ዓመት ቢኖረውም ለክለቡ የልቀቁኝ ደብዳቤ አስገብቶ እስከ አሁን መልቀቂያ ያልተሰጠው ባዬ ገዛኸኝ ለሰበታ ከተማ እንዲሁም ደግሞ ለሀድያ ሆሳዕና አሁን መፈረሙ እጅጉን አግራሞት የሚያጭር ጉዳይ ሆኗል፡፡ ባሳለፉነው ዓመት ተመሳሳይ ድርጊት ፈፅሞ የነበረው ተጫዋቹ ዘንድም ይሄን ድርጊት መፈፀሙ እጅግ አስገራሚ ሆኗል፡፡

በቀጣይ የባየ ገዛኸኝን ማረፊያ የሚወስኑ ጉዳዮችን እና የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮችን ተከታትለን የምናቀርብ ይሆናል።