የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ፋሲል ከነማ በጳጉሜ ወር ላለበት የካፍ ቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ እና ለ2014 የሀገር ውስጥ ውድድር በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዝግጅት ይገባል፡፡
በአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እየተመራ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የ2013 ቻምፒዮን መሆን የቻለው ፋሲል ከነማ ለሦስተኛ ጊዜ በአፍሪካ መድረክ ውድድር ያደርጋል፡፡ በተከታታይ ለሁለት ዓመታት በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፉት ዐፄዎቹ ዘንድሮ (2021/22) ደግሞ በሌላኛው የአፍሪካ ትልቁ ውድድር ቻምፒየንስ ሊግ ላይ ይካፈላሉ። ለዚህ ውድድርም ሆነ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጠንክሮ ለመቅረብ ይረዳው ዘንድሮ የአሰልጣኝ ሥዩም ከበደን ውል ለአንድ ተጨማሪ አመት በማራዘም እንዲሁም የወሳኝ ተጫዋቾቹ ሳማኪ ሚኬል እና ከድር ኩሊባሊን ውል ጨምሮ በድምሩ የአምስት ነባር ተጫዋቾችን ውል ሲያራዝም አስቻለው ታመነ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና ኦኪኪ አፎላቢን ማስፈረሙም ይታወሳል፡፡
ዐፄዎቹ በያዝነው ሳምንት ወደ ዝግጅት ለመግባት አስበው የነበሩ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በአንድ ሳምንት ተራዝሞ በቀጣዩ ሳምንት ወደ ዝግጅት እንደሚገቡ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ በዚህም ቅዳሜ ነሐሴ 1 ቀን 2013 ወደ ዝግጅት የሚገቡት ዐፄዎቹ መቀመጫቸውን ባህር ዳር በማድረግ በይፋ ለመጀመር እቅድ መያዛቸውን አረጋግጠናል፡፡
በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነሐሴ 17 የሚወጣው የቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ የጨዋታ ድልድልን መሠረት በማድረግ ዐፄዎቹ ከማን ጋር እንደሚገናኙ ካወቁ በኃላ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን በጳጉሜ ወር የሚያከናውኑ ይሆናል፡፡