በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በዘጠኝ ሀገራት መካከል ሲደረግ የነበረው የሴካፋ ውድድር በታንዛኒያ አሸናፊነት ተጠናቋል።
የውድድሩ የፍፃሜ ጨዋታ ከመጀመሩ ከአንድ ሰዓት በፊት የመዝጊያ መርሐ-ግብር መደረግ ጀምሯል። በዚህም የተመስገን ልጆች በሚል ስም የሚጠራው የባህል የውዝዋዜ ቡድን የተለያዩ ትርዒቶችን በማሳየት ዝግጅቱን አድምቆታል። ለ10 ደቂቃዎች ያክል ከቆየው የባህል ቡድኑ ትርዒት በኋላ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የመዝጊያ ንግግር አድርገዋል። እግርኳስ ዋንጫ ማንሳት ብቻ አይደለም ለወዳጅነት እና ለህዝብ አንድነት ይጠቅማል ያሉት ፕሬዝዳንቱ ተሳታፊ ሀገራት ባህር ዳርን እንደ ከተማቸው እንዲያዩት የባህርዳር ህዝብ ላደረገው መልካም አቀባበል እና መስተንግዶ ምስጋና አቅርበዋል። አቶ ኢሳይያስ በምስጋና ንግግራቸው አያይዘውም በውድድሩ ለተሳተፉ ሀገራት፣ ለአማራ ክልል ብሔራዊ መንግስት፣ ለአማራ ክልል ፖሊስ፣ ለአማራ ክልል ጤና ቢሮ፣ ለባህርዳር ወጣቶች ማኅበር፣ ለባህርዳር ከተማ አስተዳደር፣ ለባህርዳር ዮኒቨርስቲ፣ ለባህርዳር ህዝብ እና በዚህ ውድድር ለተገኙ ሚዲያዎች የላቀ ምስጋና ሲያቀርቡ ተደምጠዋል።
ጠንካራ ፉክክር ማስመልከት የጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ዐይን የሚይዝ ሆኖ ተገኝቷል። ቡድኖቹም የተሻለ ፍላጎት በማሳየት ሲጫወቱ ታይቷል። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ በ11ኛው ደቂቃ በንሽሚሪማና እስማኤል አማካኝነት ያደረጉት ቡሩንዲዎች እንደ ቡድን በመጫወቱ ረገድ ተሽለዋል። ቡድኑም በተጠቀሰው ደቂቃ ንሽሚሪማና አክርሮ በመታው ነገርግን ለጥቂት በወጣበት አጋጣሚ መሪ ሊሆኑ ነበር።
ኳሱን በመቆጣጠሩ ረገድ ጥሩ የነበሩት ታንዛኒያዎች ደግሞ ወደ ቡሩንዲ ሜዳ ለመድረስ ባይቸገሩም የጠራ የግብ ማግባት ሙከራ ለማድረግ እስከ 32ኛው ደቂቃ ድረስ መጠበቅ ግድ ብሏቸው ነበር። በተጠቀሰው ደቂቃም ሶስፒተር ኢዝራኤል የመጀመሪያ የቡድኑን ሙከራ ሰንዝሮ ወደ ውጪ ወጥቶበታል። ጨዋታው ቀጥሎም ቡሩንዲዎች በ35ኛው ደቂቃ ከጥሩ ቦታ የቅጣት ምት አግኝተው ነበር። የተገኘውን የቅጣት ምትም ሩኩንዶ አብዱረህማን ሞክሮት ለጥቂት ዋትቶበታል።
የቡሩንዲን የግብ ክልል መጎብኘት የያዙት ታንዛኒያዎች በ41ኛው ደቂቃም ሌላ ያለቀለት ጥቃት በኬልቪን ናፍታል አማካኝነት ሰንዝረው ነበር። ይህ ሙከራ የተደረገባቸው ቡሩንዲዎች ደግሞ የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሊጠናቀቅ አንድ ደቂቃ ሲቀረው የግብ ዘቡን ማታቻን ፈትሸው ፈትነው ተመልሰዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ ጠንከር ብለው የታዩት ቡሩንዲዎች በፈጣን ሽግግሮች፣ በቆሙ እና በተሻጋሪ ኳሶች ታንዛኒያን ማስጨነቅ ተያይዘዋል። ታንዛኒያዎች ደግሞ የመስመር ላይ አጨዋወትን አዘውትሮ በመጠቀም ግብ ለማግኘት ቢታትሩም ኳስን ከመረብ ጋር የሚያዋህድ ተጫዋች ጠፍቶ ጨዋታው 69ኛው ደቂቃ ላይ ደርሷል።
በቀጣይ ደቂቃ ግብ የሚያስቆጥር የሚመስለው የቡሩንዲ ብሔራዊ ቡድን በ69ኛው ደቂቃ እጅግ የሰላ ሙከራ አድርጎ ነበር። በዚህ ደቂቃም የአጥቂ አማካዩ መብሪዚ ኤሪክ ሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ያገኘውን ኳስ አክርሮ በመምታት ቡድኑን ቀዳሚ ሊያደርግ ነበር። ነገርግን ተጫዋቹ የመታውን ኳስ በውድድሩ ጥሩ ብቃት ሲያሳይ የነበረው ግብ ጠባቂ ሜታቻ ምናታ አክሽፎበታል።
በመሐል ዝግ ያለ ፉክክር ያሳየው ጨዋታው በመገባደጃው ላይ ዳግም ቀልብን ይዟል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ሦስት ደቂቃዎች ሲቀሩት በተደራጀ መንገድ ወደ ታንዛኒያ የግብ ክልል ያመራው የቡሩንዲ ሰራዊት እጅግ ለግብ ቀርቦ ነበር። በዚህም ክሪስፓልዲኖ ከቀኝ መስመር እየገፋ ወደ ሳጥን ይዞት የገባውን ኳስ ለሙሐመዲ ዱጁማ አቀብሎት ሙሐመዲ ለጥቂት አምልጦታል። ይህ አስደንጋጭ ሙከራ ከተደረገ ከደቂቃ በኋላ ደግሞ ታንዛኒያ ዋንጫው ጋር የሚያደርሳትን ጎል ለማግኘት ከጫፍ ደርሳ ነበር። በዚህም ኬልቪን ናፍታል ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ ገጭቶ መዳረሻው ውጪ ሆኗል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜውም ያለ ጎል ተጠናቆ አሸናፊውን ለማወቅ የመለያ የፍፁም ቅጣት ምት ተሰጥቷል። በተሰጡት የመለያ ምቶችም ታንዛኒያ ቡሩንዲን 6-5 አሸንፋ ዋንጫው የግሏ መሆኑን አረጋግጣለች።
ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ የሽልማት አሰጣት መርሐ-ግብር መከናወን ጀምሯል። በዚህም የቡሩንዲው ግብ ጠባቂ ሩኩንዶ ዋንሲሚ የውድድሩ ኮከብ ግብ ጠባቂ፣ የኤርትራው ዓሊ ሱሌይማን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቹ አቡበከር ናስር ኮከብ ተጫዋች ተብለው ከክብር እንግዶቹ ሽልማታቸውን ተረክበዋል። አቡበከር ናስር ግን ከቡድን አጋሮቹ ጋር ወደ አዲስ አበባ በትናንትናው ዕለት በማምራቱ ሽልማቱን የብሔራዊ ቡድኑ ምክትል አሠልጣኝ አስራት አባተ ተቀብሎለታል። ከግለሰቦች ሽልማት በኋላ ሦስተኛ ደረጃን የያዘችው ኬንያ እና በፍፃሜው ጨዋታ የተረታችው ቡሩንዲ ሜዳልያቸውን ተረክበዋል። በመጨረሻም የ2021 የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ዋንጫ አሸናፊ ታንዛኒያ ዋንጫውን በአምበሏ አማካኝነት ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት እና የሴካፋ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ተቀብላለች።