እስካሁን አምስት ተጫዋቾችን አስፈርመው የነበሩት ሀድያ ሆሳዕናዎች ተጨማሪ አምስት ተጫዋቾችን አክለዋል።
ኤፍሬም ዘካሪያስ አሰልጣኙን ተከትሎ ወደ ሀድያ ሆሳዕና አምርቷል፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ አዳማ ከተማ እና ወልቂጤ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ከዚህ ቀደም ወደተጫወተበት ሀዋሳ ከተማ በድጋሚ ተመልሶ የ2013 የውድድር ዓመትን ያሳለፈ ሲሆን ቀሪ የአንድ ዓመት ውል በሀዋሳ ቢኖረውም ከሰሞኑ በስምምነት ከተለያየ በኋላ አሰልጣኝ ሙለጌታ ምህረትን ተከትሎ ነብሮቹ ቤት ተጉዟል፡፡
መላኩ ወልዴ ሀድያ ሆሳዕና የተቀላቀለ ሌላው ተጫዋች ሆኗል፡፡ በ2008 ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቶ አሁን ወደ ሀድያ ሆሳዕና ካመጣው አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት ጋር አሰልጣኙ ኳስን በማቆሚያው ወቅት የመጫወት ዕድልን ያገኘ ሲሆን ሀዋሳን ከለቀቀ በኃላ ማለትም ከ2011 ጀምሮ ደግሞ ወደ ጅማ አባጅፋር ተመልሶ እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ ሲጫወት ከቀየ በኋላ ወደ ሀድያ ሆሳዕና አምርቷል፡፡
አበባየው ዮሀንስ ከሲዳማ ቡና ጋር ቀሪ የአንድ ዓመት ውል እያለው በስምምነት ከተለያየ በኃላ ማረፊያው ሀድያ ሆሳዕና ሆኗል፡፡ ይህ የቀድሞው የደቡብ ፖሊስ የአጥቂ አማካይ በሲዳማ ቡና ከ2011 ጀምሮ ላለፉት ሦስት አመታት ሲጫወት የቆየ ሲሆን አሁን ደግሞ ከዚህ ቀደም ተጫውቶ ወዳሳለፈበት ሀድያ ሆሳዕና ማምራቱ ተረጋግጧል፡፡
ኤልያስ አታሮ ሌላው ወደ ሀድያ ሆሳዕና ያመራ ተጫዋች ነው፡፡ በጅማ አባጅፋር ረጅም ጊዜያት ያሳለፈው ኤልያስ ክለቡን በአምበልነት እየመራ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ የሊጉንም ዋንጫ እንዲያነሳ አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን ከቡድኑ ጋር ተለያይቶ ማረፍያውን ሆሳዕና አድርጓል።
ግብ ጠባቂው መክብብ ደገፉም ወደ ሀድያ ሆሳዕና ተጉዟል፡፡ የቀድሞው የሀምበሪቾ ዱራሜ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ግብ ጠባቂ ወደ ወላይታ ድቻን ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ቁልፍ ሚና የነበረው ሲሆን በድጋሚ ወደ ቀድሞ ክለቡ ወላይታ ድቻ በ2012 ከተመለሰ በኃላ ጥሩ ቆይታን ማድረግ ችሏል፡፡ በወላይታ ድቻ ውሉን ከሰሞኑ ያራዝማል ተብሎ ቢጠበቅም ከዚህ ቀደም በሀዋሳ በረዳት አሰልጣኝነት ያሰለጠነውን ሙሉጌታ ምህረትን ጥሪ ተቀብሎ ነብሮቹን ተቀላቅሏል፡፡
ከአዲሶቹ ፈራሚዎች በተጓዳኝ ሚካኤል ጆርጅ ውሉን ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ፣ ደደቢት፣ ሲዳማ ቡና እና አዳማ ከተማ ሁለገብ ተጫዋች ዘንድሮ በሆሳዕና መለያ ወደ መጨረሻዎቹ የሊጉ ሳምንታት ላይ እጅግ ጥሩ የሜዳ ላይ ቆይታን ያደረገ ሲሆን ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በሀድያ ቤት ለመቆየት ፊርማውን አኑሯል፡፡