ጅማ አባጅፋር ሦስት ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የነባር ተጫዋቹን ውል አደሰ

በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ጅማ አባጅፋር ሦስት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ቡድኑ ሲቀላቅል የአንድ ነባር ተጫዋችን ውልም አድሷል፡፡

የኃላሸት ፍቃዱ ወደ ጅማ ካመሩት መካከል ነው፡፡ ይህ የፊት መስመር ተጫዋች ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ቡና የመጫወት ዕድልን ያገኘ ሲሆን ያለፉትን ሦስት ዓመታት ደግሞ በአሳዳጊ ክለቡ አዳማ ከተማ በመጫወት ከቆየ በኃላ ወደ ጅማ አምርቷል።

ሁለተኛው ፈራሚ አማካዩ አድናን ረሻድ ነው፡፡ከኢትዮጵያ ወጣቶች እና ስፖርት አካዳሚ ከተገኘ በኃላ ለካፋ ቡና እንዲሁም ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሀ በተደለደለው ወልዲያ ምንም እንኳን ክለቡ ውጤታማ መሆን ባይችልም በግሉ ጥሩ ዓመትን ያሳለፈ ሲሆን በቀጣይ ለፕሪምየር ሊጉ ክለብ አባጅፋር ለመጫወት ፊርማውን አኑሯል፡፡

ሽመልስ ተገኝ ወደ ጅማ አባጅፋር በሁለት ዓመት ውል መቀላቀል የቻለ ሌላው ተጫዋች ነው፡፡ የቀድሞው የሙገር ሲሚንቶ እና መከላከያ የመስመር ተከላካይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መጀመርያ ለመቐለ 70 እንደርታ የፈረመ ቢሆንም በአካባቢው በተከሰተው የፀጥታ ችግር መነሻነት ለስድስት ወራት ያህል ያለ ክለብ ካሳለፈ በኃላ ነበር በመጋቢት ወር አጋማሽ ላይ በአሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ወደሚሰለጥነው ሲዳማ ቡና አቅንቶ በመጫወት የቆየው። አሁን ደግሞ ቀጣይ ማረፊያው የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለው አባጅፋር ቤት መሆኑ ዕርግጥ ሆኗል፡፡

ጅማ አባጅፋር ከአዳዲስ ፈራሚዎች ባሻገር የወንድማገኝ ማርቆስን ውል ተጨማሪ ዓመት አራዝሟል፡፡ የቀድሞው የጅማ አባ ቡና ተከላካይ በአባ ጅፋር ያለፉትን ሁለት ዓመታት ያሳለፈ ሲሆን አሁንም ቆይታውን ማራዘም ችሏል።