☞”በቀጣዩ ዓመት የኢንተርናሽናል ውድድሮች በመኖራቸው ጨዋታዎች ይቆራረጣሉ”
☞”ለቀጣይ ዓመት ውድድር መስፈርት የተቀመጠላቸው ስታዲየሞቻችን ጉዳይ…”
☞”በተደጋጋሚ ስለሚነሳው ክለቦች ለተጫዋቾች ደመወዝ ያለ መክፈል ችግር እና መፍትሄው…”
☞”የሴቶቹ ፕሪምየር ሊግ ወደ እኛ የሚመጣበት ሁኔታ ይኖራል”
የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አስራ ሶስት ክለቦችን አሳትፎ ከወራት በፊት በፋሲል ከነማ አሸናፊነት መደምደሙ ይታወሳል፡፡ ካለፉት ዓመታት አንፃር በተለየ መንገድ በቀጥታ ስርጭት ታጅቦ የውድድር መዛባቶች ሳይገጥሙ የተካሄደው ውድድር በኮቪድ-19 አማካኝነት አስቀድሞ ስጋት ይታይበታል ተብሎ ቢጠበቅም ውድድሩ በተመረጡ አምስት ሜዳዎች ተከናውኖም መፈፀሙንም ጭምር በቅርቡ መመልከታችን አይዘነጋም። ከሞላ ጎደል አፈጻጸሙ የተሻለ እንደነበር የተወሳው የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቀጣዩ የ2014 ውድድር የክለቦች ቁጥር ከዚህ ቀደም ወደ ነበረበት የክለቦች ብዛት (16) ተመልሶ አሁንም በተመረጡ ክልል ስታዲየሞች ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እኛም በስፋት የተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ምን አይነት መልክ ነበረው? የቀጣዩ ዓመት የውድድር ዝግጅትስ ምን ይመስላል? በክለቦች እየታየ ያለው የደመወዝ አከፋፈል ድክመትንስ አክሲዮን ማኅበሩ ለመቅረፍ ምን አስቧል? የሚሉ እና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በማከል ሶከር ኢትዮጵያ ከፕሪምየር ሊግ ሼር ካምፓኒ የውድድር እና ሥነ-ስርአት ሰብሳቢው ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ ጋር ቆይታን አድርጋለች።
ዘንድሮ የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ካለፉት ዓመታት ውድድሮች አንፃር እጅጉን በተሻለ ተካሂዷል ማለት ይቻላል። በአጠቃላይ በአንተ እይታ የዘንድሮው የውድድር ዓመት እንዴት አለፈ? ምንስ ይመስል ነበር ?
በቅድሚያ ይሄንን ዕድል ሶከር ኢትዮጵያን ስለሰጠኝ አመሠግናለሁ። በመጀመሪያ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2013 አፈፃፀምን በተመለከተ ምን አልባት ብዙዎቻችን ሰምተናል፡፡ አፈፃፀሙም በጣም ጥሩ ነበረ፡፡ እንደ አወዳዳሪ እኛ ገና ብዙ መስራት ይቀረናል የሚል እምነት ነው ያለን ነገር ግን ጅማሮውን ስናየው ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም የነበሩት ግብረመልሶቹም የሚያሳዩት የተሻለ እንቅስቃሴ እና አፈፃፀም እንዳለ ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ኮሚቴ እኛ ይበልጥ መስራት እንዳለብን ተረድተናል። ምክንያቱም ሊጎቻችንን ከፍ ወዳለ ደረጃ ማምጣት ስላለብን የውድድር አፈፃፀም ግምገማችንን ጥሩ ነው የሚል ነገር አለን። ነገር ግን የተወሰኑ ክፍተቶች እንደነበሩብን ገምግመናል እና እንደ አጠቃላይ ስናየው ከሞላ ጎደል የተሻለ ውድድር አሳልፈናል የሚል ሀሳብ አለኝ። ይሄም የሆነበት ምክንያት ምናልባት ውድድሩ ሲመሩ የነበሩት ባለሙያዎች ከካምፓኒው ጀምሮ የውድድር ሥነ-ስርአት እና ፕሪምየር ሊጉን በዳኝነትም በኮሚሽነርነትም ሲያገለግሉ የነበሩ የተሻሉ እና በሀገራችንንም አሉ የሚባሉ ስለሆኑ ነው።
የዘንድሮ ውድድሩ ከሞላ ጎደል በጥሩ ሁኔታ ተጠናቋል ማለት ይቻላል። ነገር ግን የቀጣይ ዓመት ውድድር የዝግጅት ሁኔታ በምን መልክ እየሄደ ነው? የ2014 ዝግጅታችሁስ ምን ይመስላል ? ምንስ እየሰራችሁ ነው?
እንግዲህ ቅድም እንደገለፅኩት የዘንድሮ ዓመት የውድድር አፈፃፀማችን ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ነው ብለን ስናስብ ግን ክፍተቶች አልነበሩብንም ማለት አደለም። ነገር ግን በአብዛኛው የሰራናቸው ስራዎች ክለቦቻችንን ማብቃት ነው፡፡ ክለቦቻችንን ማብቃት ማለት ለምሳሌ እንውሰድ እና የውድድር ሜዳዎቻችን በአብዛኛዎቻችን እንዳየናቸው በተመረጡ ሜዳዎች መደረጉም እንዳለ ሆኖ እነዛ የተመረጡ ሜዳዎች ምን ያህል ለቀጥታ ስርጭት ምቹ ነበር የሚለውን ለማየት ችለናል። ለምሳሌ ብዙ ክፍተት የነበረባቸው ሜዳዎች ነበሩ፡፡ለቀጣዩ ግን ምንድነው ያደረግነው ምናልባት ከዚህ በፊት ዕድሉን ምንሰጠው ለክለቦች ነው እነዛ ክለቦች ከሚኖሩት ክልል ጋር ግንኙነት አድርገው ሜዳዎችን ለማዘጋጀት የሚያስፈልጉ እና ሜዳውን ሲያዘጋጁም መሟላት ያለባቸው ከተሞች ማሟላት ያለባቸውን ዝርዝር ጠቅሰን ደብዳቤ ልከናል። ለሁሉም ክለቦች በተላከው መስፈርት መሰረት እንደ አምናው ምናልባት እኛ ሄደን የምናዘጋጅበት ምክንያቶች አይኖሩም። የተሻሉ እና ያንን መስፈርት የሚያሟሉ ከተሞች እና ሜዳዎች ውድድሩን ያዘጋጃሉ የሚል እምነት አለን። ያንንም ለማድረግ ደብዳቤዎች አዘጋጅተን ልከናል እነዛ ደብዳቤዎችም መስፈርቶች ናቸው፡፡ እነዛን መስፈርቶችንም አይተው ማሻሻል ያለባቸውን ምናልባት አምና ካከናወንባቸው ሜዳዎች ውስጥ ያንን ሊያሟሉ የሚችሉ እና ጥቂት ማስተካከል ያለባቸው ሜዳዎች አሉ እነዛ እነዛን አስተካክለው ይቀርባሉ የሚል እምነት አለን እና ይሄን ይሄን እየሰራን ነው፡፡ ከዚህም በተረፈ የውድድር ደንቦችን እና የማስፈፀሚያ ሰነዶችን እየሰራን ነው፡፡ ኮሚቴው ውድድሩ ከተጠናቀቀ ጀምሮ በስራ ላይ ነው ያለው። ምንም እንኳን ይፋዊ የሆነ የስራ መግለጫዎችን ባንሰጥም ስራዎችን መስራት ከጀመርን ቆይተናል፡፡ ደንቦች እያዘጋጀን ነው፡፡ምናልባት በቅርቡ ደግሞ በቢሮ በኩል ለክለቦች ስልጠና ይሰጣሉ ክለቦቻችን ምን አይነት የብራንዲንግ ሲስተም፣ ማርኬቲንጋቸውስ ምን ይመስላል፣ በምን መልኩስ ነው ክለቦች ገቢ ሊያገኙ የሚችሉት የሚሉ ጉዳዮችን ያቀፈ ስልጠና ለክለብ አመራሮች ስልጠናዎችን ለማዘጋጀት አስበናል። የአሰልጣኞችንም ስልጠና እንደዛው ከሚመለከታቸው አካላቶች ጋር እየተነጋገርን ነው፡፡ ለፕሪምየር ሊግ አሰልጣኞቻችን እና ለዳኞቻችንም የማሻሻያ ስልጠና እንዲሰጡ ከሚመለከታቸው የዲኤስቲቪ እና የቤትኪንግ ድርጅት አመራሮች ጋር በቢሮ በኩል ግንኙነት እየተደረገ ነው፡፡ እነዚህ እነዚህ የጠቀስኳቸው ስልጠናዎች በኦፍ ሲዝን የሚሰጡ ስልጠናዎች ናቸው። እነዚህን በዚህ ክረምት እና በተለያዩ የእረፍት ጊዜያቶች ተግባራዊ ለማድረግ ተዘጋጅተናል እንደ አጠቃላይ በቀጣዩ ዓመት የተሻለ የውድድር ጊዜ ይኖረናል የሚል እምነት አለን፡፡
ቅድም በንግግርዎ መሐል ከተጠናቀቀው የውድድር ዓመት በቀጣይ የተሻለ ውድድር እንደሚኖር በተደጋጋሚ ሲገልፁ እየሰማሁ ነበር እና የተለየው ነገር ምንድነው? የ2013 የቤትኪንግ ፕሪምየር በአምስት ሜዳዎች ተደርጎ ነበር ይሄ ቁጥር ከሜዳ ጥራት ጋር ተያይዞ ቁጥሩ ይቀንሳል ይባላል በዚህ ዙሪያስ ያለዎት ሀሳብ ምን ይሆን?
ምናልባት የተለዩ መስፈርቶች ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በአምናው አፈፃፀማችን ላይ እንደ ክፍተት ያየናቸው ነገሮች አሉ። አንዳንድ ሜዳዎች ምናልባት ለቀጥታ ስርጭት የማይመጥኑ እንደነበሩ ለማየት ችለናል፡፡ ነገር ግን እነዛ ሜዳዎች ይቀራሉ ማለት አይደለም ለተቀመጠው መስፈርት በቂ የማስተካከያ ጊዜ ስላላቸው የተቀመጠውን መስፈርት ካሟሉ የማይመረጡበት ምክንያቶች አይኖሩም። ሌላው የሚቀጥለው ዓመት ምናልባት ትንሽ ቻሌንጅ ይገጥመናል ብለን የምናስበው የኢንተርናሽናል ውድድሮች ብዙ አሉን። ለምሳሌ ብሔራዊ ቡድናችን ለአፍሪካ ዋንጫ አልፏል በዛች ወቅት የአንድ ወር እረፍት በውድድሩ ምክንያት ሊኖረን ይችላል፡፡ ከዛ በተጨማሪ የአለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች አሉ በዛን ወቅትም የሚቆራረጥበት ሁኔታዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡እነዛን ባማከለ እና እነዛን ክፍተቶች እንደ ትራንዚሽን የምንጠቀምበት ከከተሞች ከተሞች የምንዘዋወርባቸውን ጊዜያቶች በእነኚህ የእረፍት ጊዜያቶች ላይ ለማድረግ እና የመቆራረጦቹን ነገሮች ለመቀነስ እንሞክራለን የሚል እምነት አለን። የሚቀጥለው ውድድር ሌላው ለየት የሚያደርገው ምናልባት ዘንድሮ ያደረግነው በአስራ ሦስት ክለቦች ነበር፡፡ በቀጣይ ግን የምናደርገው በአስራ ስድስት ክለቦች ስለሆነ በአንድ ከተማ ከዚህ በኋላ የምናደርገው ቆይታ ረዘም ሊል ይችላል፡፡በዛን ሰአት ምናልባት የመወዳደሪያ ሜዳዎች ያንን በዛ ያለ የጨዋታ ቁጥርን ለማስተናገድ የሚችሉ መሆን አለባቸው። በነገራችን ላይ ለክለቦች ደብዳቤ የፃፍንላቸው እና እነዚህን መስፈርቶች የሚያሟሉ ሜዳዎች ከመጡ የውድድር ሜዳዎቻችን ሊጨምሩ ይችላሉ፡፡ አምና ከነበረውም ሊቀንሱ የሚችሉበት ሁኔታም ይኖራል እና በአጠቃላይ በዚህ መልኩ ነው እየተዘጋጀን ያለነው፡፡
ለአንድ ውድድር ድመቀት ከሆኑ ነገሮች መካከል ደጋፊዎች ዋነኞቹ ናቸው፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ደግሞ በኮቪድ-19 የተነሳ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ገብተው ጨዋታዎችን መመልከት አልቻሉም፡፡ እንደ ምንሰማውም የተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለይ በአውሮፓ ዋንጫም በሀገራችን ሴካፋንም ጨምሮ ወደ ስታዲየም ደጋፊዎች እንዲመለሱ እየተደረገ ነው፡፡ እንደ ሊግ ካምፓኒ በቀጣይ ወደ ሜዳ ደጋፊዎች እንዲመለሱ ምን እየተሰራ ነው?
እንዳልከውም የስታዲየሞቻችን ጌጦች ደጋፊዎቻችን ናቸው፡፡ የእግርኳሱ ደጋፊዎች ወደ ሜዳ ቢገቡልን እና ያንን የቀጥታ ስርጭት ይበልጥ ያማረ ያደርጉልናል ብለን እናስባለን። ምናልባት ሀገራችን እያስተናገደች ባለችሁ ሴካፋ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እየተወዳደረ ነበር፡፡ በዚህም ውድድር ላይ ደጋፊዎች እንዲገቡ ተፈቅዷል፡፡ ለዚህ የሴካፋ ዋንጫ ደጋፊ እንዲገባ እስከተፈቀደ ድረስ በቀጣዩ ዓመት በሚደረገው የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ላይ ደጋፊ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ። የስታዲየሙ አንድ አራተኛ የሚሆን ደጋፊ በባህርዳር ገብቶ እየተከታተለ ነበር፡፡ ይሄ በመሆኑ ደግሞ በቀጣይ ለእኛም ከመንግስት ጋር በሚኖረን ግንኙነት ይፈቀዳል ብለንም እናምናለን። በቅርቡ በነበረው የመዝጊያ ሥነ-ስርአትም ላይ የተከበሩ መቶ አለቃም ገልፀውታል፡፡እሳቸው እንዳሉትም ደጋፊዎቻችን ወደ ሜዳ አለመግባታቸው ክለቦች ከደጋፊዎች ሲያገኙት የነበረው ገቢ መቀነሱ በክለቦቻችንም ላይ የገቢ መቀነስ አምጥቷል፡፡ ይሄንን ችግር ለመቀነስ መንግስት ይፈቅድልናል የሚል እምነት አለን። የኮቪድን ስርጭት ባማከለ መልኩ ስታዲየሙ ከሚይዘው አንድ አራተኛም ሆነ ካለውም የስታዲየሙ አቋም አንፃር የሚቀጥለው ዓመት ላይ ደጋፊዎቻችን ወደ ሜዳ ይመጡና የቀጥታ ስርጭቱ ይበልጥ ተወዳጅ ያደርገዋል የሚል እምነት ነው ያለን፡፡
ካለፉት ዓመታት አንፃር የተሻለውን የሊግ ውድድር ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን ውድድሩ በጥሩ መልኩ ቢካሄድም ክለቦች ለተጫዋቾቻቸው ደመወዝ መክፈል እያቃተቸው የውድድሩን ገፅታም በተወሰነ መልኩ የሚያጠለሹ ሁነቶችን እያስተዋልን ነበር፡፡ ሊግ ካምፓኒውስ ከደመወዝ አከፋፈል ጋር ስለሚፈጠሩ ክፍተቶች ምን ሀሳብ አለው? በዚህ ላይስ ያሰባችሁት ዕቅድ ይኖራል?
ምንአልበት የተጫዋቾችን ደመወዝ በተመለከተ የሊግ ካምፓኒው የመወሰን ስልጣን ባይኖረውም ነገር ግን ከሊጉ ጥራት እና ተቀባይነት አንፃር የሚያደበዝዝ ገፅታን ከመፍጠር አንፃር ደመወዝ ባለመክፈል እና ክለቦች ይመጣሉ አይመጡም የሚለውን ስጋት ምናልባት በ2013 ትልቁ የነበረ ቻሌንጅ ነበር። የቀጥታ ስርጭት ላይ እንደዚህ አይነት ክፍተቶች ሲፈጠሩ በሊጉ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ አለ፣ ጥቁር ጠባሳ ሊያመጣ ይችላል የሚል ስጋት ሁሉ ነበር። አምና ካሳለፍናቸው ተግዳሮቶች ዋነኛው ይሄ ነበር፡፡ በቀጣይ ግን እኛ ያሰብናቸው ነገሮች አሉ። በደንባችን ላይ የምናካትታቸው ይሆናሉ። በቀጣይ በጠቅላላ ጉባኤ የሚወሰን ይሆናል ምናልባት ወቅቱ ሲደርስ የምናሳውቀው ቢሆንም ክለቦቻችን ዓመቱን ሙሉ ደመወዝ መክፈል የሚያስችላቸውን ዋስትና ሊያመጡ ይገባል፡፡ ይሄም ክለቦች ለውድድር ሲመዘገቡ ኦዲት የተደረገ ፋይናሽናል አቅም በሚያቀርቡበት ሰአት አመቱ ውስጥ ደመወዝ ከፍለው ውድድሩን ሊጨርሱ ይችላሉ ? ወይንስ አይችሉም ? የሚለውንም ለመወሰን እና ለማየት ስለሚያስችለን እንደነዚህ አይነት መንገዶችን በቅርቡ ለማየት በታሳቢነት የተያዘነ ነገር አለ። ነገር ግን ይሄን እና ተያያዥ ጉዳዮች ያው ጠቅላላ ጉባኤው ሊያፀድቀው ይገባል እና እነዚህ ነገሮች ጊዜው ሲደርስ የምንገልፃቸው ይሆናል፡፡ በእርግጠኝነት የሚቀጥለው ዓመት ስጋት ነው ብዬ የማስበው አንዱ አሁንም የደመወዝ አከፋፈል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ይነስም ይብዛም አምና ላይ የነበረ የ50ሺህ ብር ገደብ ነበረ አሁን ደግሞ ይሄ ገደብ ተነስቷል፡፡ ክለቦች አሁን በስሜት ከሚጠበቀው በላይ ለፊርማ እና ለደመወዝ ሲያወጡ እየሰማን ነው፡፡ ክለቦች ለተጫዋቾች የሚገቡት ቃል እና የሚከፍሉት ገንዘብ አመቱን ሙሉ ላያስጨርሳቸው የሚችል በጀት ላይ እንዳይወድቁ ስጋት አለኝ። ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ላይ ክለቦቻችን ከወዲሁ በጥንቃቄ ቢጓዙ የተሻለ ነው የሚል እምነትም አለኝ። ሀምሳ ሺው መነሳቱ ለእኔ ስጋት ነው። ለተጫዋቾቹ በአንድ በኩል ጥቅም ነው። ለክለቦቻችን ግን አመቱን በወጥነት ከመጨረስ አንፃር ስጋት የሚፈጥር ነገር ይኖራል እና እንደ እኛ ግን በእነዚህ ላይ የተለያዩ ስራዎች ለመስራት በዝግጅት ላይ እንገኛለን፡፡
ቅድም የነካኩት ሀሳብ ነበር። በተለይ በዚህ ክረምት እና በተለያዩ የእረፍት ወቅቶች ስልጠናን ለመስጠት እንዳሰባችሁ። ስልጠናው በዋናነት ምን መልክ አለው ? እነማንንስ ነው ለማሰልጠን በእቅድ የያዛችሁት ?
በአሁኑ ሰአት እነዚህን ተፈፃሚ ለማድረግ በንግግር ላይ ነው ያለነው፡፡ ስልጠናውን ስንጀምር ከክለብ አመራሮች ነው። የምንጀምረው የክለብ አመራሮች ከክለብ አስተዳደር ጀምሮ ከክለብ አወቃቀር፣ የክለብ ብራንዲግስ ምን ይመስላል፣ ክለብን ወደ ገበያ ማውጣት እንዴት ይቻላል፣ የማርኬቲንግ ፅንሰ ሀሳባቸው ምን ይመስላል የሚለውን ከክለብ አመራሮች ጀምሮ በመቀጠል ለዳኞቻችንም የተወሰኑ ስልጠናዎችን መስጠትም ያስፈልጋል፡፡እንደ ውድድር እና ሥነ-ስርአት አምና ያደረግነው አንድ ስልጠና ነበር። ደንብን እና አዳዲስ ህጎችን በተመለከተ ምናልባት ዘንድሮ ላይ ታስተውሱ እንደሆነ በዩሮ ሀያ ሀያ ላይ የተከሰተ አስደንጋጭ ክስተት ነበር። የኤሪክሰን ጉዳት ይሄን ከተመለከትን በኋላ ተጫዋቾች የፈርስት ኤይድ እውቀት ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነት አለን። ለተጫዋቾች ብቻ አደለም ክለብ ላይ ያሉ የህክምና ባለሙያዎች እንዴት ናቸው ብቁ ናቸው የሚለውን ነገር ለማሳደግ የሪፍሬሽመንት ኮርስ ያስፈልጋቸዋል የሚል እምነት አለን። እንደ ውድድር እና ሥነ ስርአት እነዚህ አይነት ስልጠናዎችን አካተን የሚመለከታቸው ባለሙያዎች እንዲሰጡ በተጨማሪም ዳኞቻችን ላይስ ምን አይነት ስልጠና ያስፈልጋሉ የሚል በእቅድ የተያዘ ነገር አለ። ይሄ እቅድ ምናልባት ተግባራዊ የሚሆነው ቅድም እንዳልኩት ጠቅላላ ጉባኤው የሚወስነው ይሆናል ይሄን ለማድረግ በጀት ስለሚነካው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀርቦ የሚያፀድቀው ስለሆነ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ስልጠናውን ይወስዳሉ ብለን እናስባለን አምና ካደረግነው በተጠናከረ መልኩ ማለት ነው፡፡አምና እንደውም ለአፈፃፀሙ ጥሩ ካሰኙት አንዱ ቅድመ ስልጠናዎች ናቸው፡፡ ከውድድሩ በፊት የተደረጉ አስራ ሶስቱም ክለቦች ከተጫዋች እስከ አመራር ከአሰልጣኝ እስከ ስራ አስኪያጅ ሁሉም ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ በወቅቱ ስልጠናዎቹ ያተኮሩት በደንብ እና በአዳዲስ ህጎች ላይ ነበር። ነገር ግን ዘንድሮ ላይ የአመራሮቹ ለብቻ ከዲኤስቲቪ ጋር በመተባበር የሚሰጡ ስልጠናዎች አሉ። ስለ ክለብ ብራንዲግ ክለብ እንዴት ነው ለገበያ ማብቃት የሚቻለው እንዴት ነው ማለያን ለገበያ ማቅረብስ የሚችሉት ማለያ ላይ የሚፃፉ የገቢ ማስገኛ ስልቶች ምን ይመስላሉ የሚሉትን ከዲኤስቲቪ እና ከቢሮአችን ጋር በመተባበር የሚሰጡ ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ ለክለቦች፣ ለአሰልጣኞች እና ቅድም ላልኳቸው ስልጠናዎቹ መቼ ይሆናሉ የሚለውን በውል አልተቀመጠም በንግግር ሂደት ላይ ነን ለአሰልጣኞቻችን ግን ከውጪ የሚመጡ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ለማሰጠት እየጠየቅን ነው፡፡ ያም ያሳየን ብልጭታ አለ ይሰጣል የሚል እምነት አለን የአሰልጣኞቻችን ዝርዝር አስተላልፈናል ለዲኤስቲቪ ዋናው ቢሮ የዋና አሰልጣኝ የምክትል እና የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች ዝርዝርን ያላቸውን የትምህርት ዝግጅት እና የአሰልጣኝነት ዝግጅትን በሙሉ በመግለፅ አስተላልፈናል እና አሁን መቼ ይሰጥ እና ማን ይስጠው የሚለውን እነሱ ወስነው እስኪያሳውቁን ነው እንጂ ከቅድመ ውድድር ዝግጅት በፊት በዚህ ክረምት በአብዛኛው ስልጠናውን እንሰጣለን ብለናል፡፡
ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ በወንዶቹ በኩል እየተደረገ ይገኛል፡፡ በአንድ ወቅት እንደሰማሁት የሊግ ካምፓኒው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽንን የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮንን እናወዳድር የሚል ጥያቄ አንስታችሁ ነበር። ይሄ ሀሳብ ከምን ደረሰ ?
የሴቶችን ፕሪምየር ሊግን በተመለከተ ወደ ሴቶቹ ከመሄዳችን በፊት የወንዶቹ ፕሪምየር ሊግ በራሱ እንዲተዳደር እና በራሱ እንዲቆም ትልቁን ድርሻ የወሰዱት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽን እና ክለቦች ናቸው፡፡ አሁንም ክለቦች የሚጠይቁ ከሆነ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌድሬሽንም አወንታዊ መልስ የሚሰጥ ከሆነ የሴቶቹ ፕሪምየር ሊግ ወደ እኛ የሚመጣበት ሁኔታ ይኖራል የሚል እምነት አለኝ። ነገር ግን አሁን እዚህ ጉዳይ ላይ የተሄደበት እርምጃ ያለ አይመስለኝም እስከ አሁን ባለኝ መረጃ ምንም እየተሰራ እንዳልሆነ ነው የሚገባኝ፡፡