የጣና ሞገዶቹ ነገ ከአዲሱ አሠልጣኛቸው ጋር ይፈራረማሉ

አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን የሾሙት ባህር ዳር ከተማዎች ነገ ከሰዓት በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ ከአሠልጣኙ ጋር ስምምነት ይፈፅማሉ።

በተጠናቀቀው የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ደረጃን ይዘው የጨረሱት ባህር ዳር ከተማዎች ከአሠልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ጋር በስምምነት ከተለያዩ በኋላ በቀጣይ ዓመት ተጠናክሮ ለመቅረብ ዝግጅት እያደረጉ ይገኛሉ። በዋናነት በሰበታ ከተማ የውድድር ዓመቱን የቋጩትን አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን የግሉ ለማድረግ ሲጥር የነበረው ክለቡም በመጨረሻ ውጥኑ ሰምሮ አሠልጣኙን በሁለት ዓመት ውል ወደ ስብስቡ አምጥቷል።

ሶከር ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት ድርድሮች እና ንግግሮች ፍሬ ማፍራታቸውን ገልፃ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ በሚሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ነገሮች ይፋ እንደሚሆን ማመላከቷ የሚታወስ ሲሆን አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱም ነገ 8:00 ገርጂ አካባቢ በሚገኘው ኔክሰስ ሆቴል በይፋዊ ጋዜጣዊ መግለጫ እና የፊርማ ሥነ-ስርዓት የሁለት ዓመት ውል እንደሚፈፅሙ ተረጋግጧል።

ዓርብ ወደ ባህር ዳር አምርተው የነበሩት አሠልጣኙም ምንም እንኳን እስካሁን ስምምነታቸው በቃል ደረጃ ብቻ ቢሆንም ክለቡ የፈፀማቸው ዘጠኝ ዝውውሮች ላይ ተሳትፎ እንደነበራቸው ሰምተናል። ነገ በሚኖረው ሥነ-ስርዓትም ዝርዝር የስምምነቱ ጉዳዮች ለብዙሃን መገናኛዎች እንደሚብራራ ይጠበቃል።

ያጋሩ