አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱን ዋና አሠልጣኝ አድርገው የሾሙት የጣና ሞገዶቹ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረውን አዳነ ግርማን በምክትል አሠልጣኝነት ለማምጣት ንግግር ጀምረዋል።
በአሁኑ ሰዓት ከአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ ጋር የሁለት ዓመት ውል እየተፈራረሙ የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች የምክትል አሠልጣኝ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በአዲሱ ዋና አሠልጣኝ አብርሃም በተሰጠው ማብራሪያም ከእርሳቸው ጋር የቀድሞ አንጋፋ እና ባለ ታሪክ ተጫዋቾችን በምክትልነት ለማምጣት ያቀረቡት ጥያቄ በቦርዱ አዎንታዊ ምላሽ ማግኘቱን ገልፀው አዳነ ግርማን ለማምጣት ንግግር መጀመራቸውን አስረድተዋል።
የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ዋልያዎቹ ባለታሪክ ተጫዋች አዳነ ጫማ ከሰቀለ በኋላ 2012 ላይ ወደ ወልቂጤ ከተማ በማምራት በምክትል አሠልጣኝነት ማገልገሉ ይታወሳል።
በተያያዘ ከአዳነ ግርማ ውጪ ሌሎች አንጋፋ እና ባለ ታሪክ ተጫዋቾችን በአሠልጣኝ ቡድን ውስጥ ለማስገባትም ንግግር ላይ መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን ከክለቡ ጋር ውል ያላቸው የአሠልጣኝ ቡድን አባላትም በስራቸው እንደሚቀጥሉ ተገልጿል።