ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና በሁለት ከተሞች ይደረጋል

ክለቦች እና ክልሎችን በማጣመር ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚደረገው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና በነሐሴ ወር አጋማሽ በሁለት ከተሞች ይደረጋል፡፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ላለፉት ሦስት ዓመታት ሳያካሂድ የቆየው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ዘንድሮ ከክለቦች ባሻገር ክልሎች ተካፋይ በማድረግ የ2013 የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ሻምፒዮና በሚል በሁለት ከተሞች እንዲደረግ ተወስኗል፡፡ ከትግራይ ክልል ውጪ ያሉ ክልሎች እና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች የውስጥ ውድድርን እስከ ሐምሌ አጋማሽ ድረስ ሲያከናውኑ የነበረ ሲሆን በተካሄዱ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከ17 ዓመት በታች ውድድር አንደኛ ሆነው ያጠናቀቁ ብቻ በዚህ ውድድር ላይ ይሳተፋሉ። እስከያዝነው ሳምንት ድረስ ደግሞ በክለብ ደረጃ ታቅፈው በተመሳሳይ በውስጥ ውድድር ላይ ሲሳተፉ የነበሩ ክለቦች ምዝገባን የሚያከናውኑ ሲሆን ውድድሩም ከነሐሴ 15 እስከ ጳጉሜ 3 2013 ድረስ በባቱ (ዝዋይ) እና አዳማ ከተማ እንዲከወን ፌዴሬሽኑ ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡

ለዚህም ውድድር ምዝገባ ያደረጉ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ቅዳሜ ነሐሴ 1 በጁፒተር ሆቴል ከረፋዱ 3፡00 ጀምሮ ቅድመ ውድድር ስብሰባ ላይ ተወካያቸውን ይዘው እንዲገኙ ፌዴሬሽኑ ለክለቦች በላከው ደብዳቤ አሳውቋል፡፡