​በሴካፋ ውድድር ከደመቀው ዓሊ ሱሌይማን ጋር የተደረገ ቆይታ

👉“ኩን አጉዌሮን በጣም ነበር የማደንቀው”

👉”… ስደት መጥፎ ነገር ነው።”

👉”ስለኢትዮጵያ ያለኝ አመለካለት ጥሩ ነው። ህዝቡም በጣም ደስ የሚል ነው”

የምስራቅ እና መካከለኛው የአፍሪካ ከ23 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት ከቀናት በፊት በታንዛኒያ አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወቃል። ምንም እንኳን በውድድሩ ላይ የኢትዮጵያ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አመርቂ ውጤት ባያመጣም የቡድኑ አምበል አቡበከር ናስር የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ተብሎ የግል ክብር አግኝቷል። ከግል ክብር ጋር በተያያዘ በኤርትራ ቴክኒካል ዳይሬክተር ዳንኤል የሚመራው የኤርትራ ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን የፊት መስመር የሚመራው ዓሊ ሱሌይማን ኢትዮጵያ ላይ ባስቆጠራቸው አራት ጎሎች የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ሽልማት ተበርክቶለታል። በውድድሩ የብዙዎች ቀልብን የገዛው ተጫዋቹንም ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታ አጭር ቆይታን አድርጋለች።

በቁመቱ አጠር ያለው ነገርግን ፈጣን እና ቀልጣፋው ዓሊ ውልደቱ ሳውዲ አረቢያ ጅዳ ከተማ ነው። ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትሮች በላይ ተጉዘው ከኤርትራ ወደ ሳውዲ ያመሩት ቤተሰቦቹም በጅዳ ከተማ የስደት ህይወታቸውን ከገፉ በኋላ የመጨረሻ ልጃቸውን በወለዱ በአራት ወራቸው ‘የሰው ሀገር በቃን’ ብለው ዳግም ወደ ኤርትራ ተመልሰዋል። እንደ ወላጆቹ “ስደት መጥፎ ነገር ነው” የሚለው ዓሊ የአራት ወር ጨቅላ እያለ ኤርትራ ከመጣ በኋላ እድገቱን በሰንዓፌ ከተማ አድርጓል። የቤቱ አምስተኛ ልጅ የሆነው ዓሊም ኢብራሒም፣ ሀሰን፣ አብደላ እና መሐመድ የተባሉ ወንድሞች እንዳሉት ያወሳል።

እንደ አብዛኛው ታዳጊ በሰፈር ውስጥ እግርኳስ መጫወት የጀመረው ተጫዋቹም በዋናነት በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ ፍቅሩን ለማስታገስ ጊዜውን ከኳስ ጋር ያሳልፍ እንደነበር ያስታውሳል። በተለይ ታላቅ ወንድሙ ኢብራሂም እግርኳስ ተጫዋች ስለነበር እርሱን እያየ እንዳደገ ይመሰክራል። በትምህርት ቤት ጨዋታዎች ላይ መጫወት ካዘወተረ በኋላም በርዕሰ መዲናው ላይ ለሚደረግ የዞን ውድድር በመታጨት በ16 ዓመቱ ወደ አስመራ ያመራል። በዚህም ዞባ ደቡብ የሚባል ቡድንን በመወከል ባሳየው ምርጥ ብቃት የኤርትራ ክለቦች ዐይናቸውን ይጥሉበታል። በውድድሩ ባሳየው ብቃት ከሦሰት በላይ ክለቦች ፍላጎት ቢያሳዩም ቀይ ባህር የተባለው ክለብ ጠንከር ያለ ፍላጎት አሳይቶ የ16 ዓመቱ ተጫዋች መዳረሻው እዛ ይሆናል።

ቀስ በቀስ ራሱን እያጎለበተ የመጣው ተጫዋቹም ሀገሩን የመወከል ዕድል አግኝቶ ለ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ጥሪ ቀረበለት። በዚህ የእድሜ እርከን ብሔራዊ ቡድን ውስጥም በመሆን በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተከናወነው የሴካፋ ውድድር ላይ ተሳትፎ አደረገ። ከ20 ዓመት በታች ቡድን በመቀጠል ደግሞ በኦሊምፒክ ቡድን (ከ23 ዓመት በታች ቡድን) ውስጥ እንዲካተት ተደርጎ ከቀናት በፊት በተጠናቀቀው እና ሀገራችን ባስተናገደችው ሌላ የሴካፋ ውድድር ላይ ተሳታፊ ሆነ። በውድድሩም ድንቅ ብቃቱን በማሳየት አራት ግቦችን ከመረብ በማሳረፍ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ራሱን ለኢትዮጵያዊያን አስተዋውቋል።

ከልጅነቱ ጀምሮ ታላቅ ወንድሙን (ኢብራሂም) እያየ ያደገው ዓሊ ጎል ፊት አይምሬ አጥቂ የመሆን ፍላጎት እንደነበረው ይናገራል። ይህ ፍላጎቱ ስኬታማ ሆኖም ከአሁኑ የሴካፋ ውድድር ውጪ በሁለት ዓመታት በሀገሩ ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል። ከታላቅ ወንድሙ በተጨማሪ ደግሞ ዓሊ የአርጀንቲናዊው አጥቂ ኩን አጉዌሮ አድናቂ እንደሆነ እና በአጨዋወቱ ላይ አጉዌሮ ተፅዕኖ እንዳደረገበት ያወሳል። “ልጅ እያለው ታላቅ ወንድሜ ተጫዋች ስለነበር እርሱን ነበር የማየው። እርሱ ሲጫወት በአፅንኦት እከታተለው ነበር። በእግርኳስ ህይወቴ ላይም የእርሱ ተፅዕኖ ከፍተኛ ነበር። ከእርሱ በተጨማሪ ደግሞ አርጀንቲናዊውን አጥቂ ኩን አጉዌሮን በጣም ነበር የማደንቀው። አጉዌሮ በእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ሲጫወት እመለከተው ነበር። እርሱ የሚያደርገውን ነገርም እከታተል ነበር። ስለምወደውም አጨዋወቱን እኮርጅ ነበር።”

ያደረግነው ቆይታ ቀጥሎም ስለ ኢትዮጵያ እግርኳስ ያለውን እውቀት ጠየቅኩት። ዓሊም ፈጠን ባለ የትግረኛ ንግግሩ ተከታዩን ሀሳብ መናገር ጀመረ። “እውነት ለመናገር ትንሽ እያለሁ ስለ ኢትዮጵያ ብዙ አላውቅም ነበር። አሁን ግን በተለያየ መንገድ ስለ ኢትዮጵያ እሰማለሁ። አያለሁም። ስለተጫዋቾች፣ ስለደጋፊዎች እና ስለአጨዋወት የተወሰነ ዕውቀት አለኝ። በተለይ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ዲ ኤስ ቲቪም ሊጋችሁን ያሳይ ስለነበር የኢትዮጵያን እግርኳስ እከታተል ነበር። በዋናነት ደግሞ ሮቤል ኢትዮጵያ ቡና ይጫወት ስለነበር ስለ ኢትዮጵያ ይነግረን ነበር። በአጠቃላይ ስለኢትዮጵያ ያለኝ አመለካለት ጥሩ ነው። ህዝቡም በጣም ደስ የሚል ነው።”

ከወራት በፊት የብሔራዊ ቡድን አጋሩ ሮቤል ወደ ኢትዮጵያ ቡና ሲዘዋወር ከቡናማዎቹ ጋር ስሙ ተያይዞ የነበረው ዓሊ ያ ወሬ ተጨባጭ እንዳልነበር እና ክለቡ አግኝቶት ምንም እንዳላወራው ይናገራል። አሁን ግን ተጫዋቹ ከቀይ ባህር ክለብ ጋር የአንድ ዓመት ውል ቢቀረውም ለባህር ዳር ከተማ ፊርማውን ለማኖር በግል ተስማምቷል። በቅርቡም ከክለቡ ጋር ተነጋግሮ የጣና ሞገዶቹን በይፋ የሚቀላቀልበት መንገድ ኤርትራ ከገባ በኋላ እንደሚያመቻች አስረድቶናል።

በሀገራችን በተደረገው የሴካፋ ውድድር ላይ ደምቆ የታየው ተጫዋቹም በውድድሩ ስላሳየው ብቃት የሚለው አለው። “በሴካፋ ውድድር ስሳተፍ ይህ የመጀመሪያዬ አይደለም። በዩጋንዳ አስተናጋጅነት በተከናወነው ውድድር ላይም ሀገሬን ወክያለሁ። ከዛም ውድድር ተሞክሮ ወስጄ ነበር። በዘንድሮ ውድድር ላይ ደግሞ እንዳያችሁት ጥሩ ብቃት አሳይቻለሁ። አሠልጣኞቼ በሚነግሩኝ ነገር እንዲሁም ከቡድን አጋሮቼ ጋር በመተባበር የተሻለ ነገር አሳይቻለሁ።” ይላል።

ወደፊት ይበልጥ ጎልብቶ የሀገሩን ስም ለማስጠራት ራዕይ ያለው ተጫዋቹ ከኢትዮጵያም አልፎ እስከ አውሮፓ በመጓዝ የመጫወት ፍላጎት እንዳለው ያብራራል። ተጫዋቹም በኤርትራ እንዲሁም በሴካፋ ውድድር አይተውት ላበረታቱት የኢትዮጵያ ደጋፊዎች ምስጋና አቅርቦ ሀሳቡን ቋጭቷል።