በካፍ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ ተካፋይ የሆነው ኢትዮጵያ ቡና ለቅድመ ውድድር ዝግጅት ወደ ቢሸፍቱ ሲያመሩ የቡድኑ አሰልጣኞች አብረው አልተጓዙም።
በአሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ የሚመሩት ኢትዮጵያ ቡናዎች በመጪው የውድድር ዘመን ላሉባቸው አህጉራዊ እና ሀገራዊ ውድድሮች ቅድመ ዝግጅታቸውን ለማድረግ ዛሬ ከሰዓት ለቡ ከሚገኘው የክለቡ የተጫዋቾች መኖርያ በመነሳት ወደ ቢሸፍቱ ከተማ አቅንተዋል።
ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ተጫዋቾችን ጨምሮ በጥቅሉ ከ35 በላይ ተጫዋቾች ይዘው ወደ ሥፍራው ያቀኑት ቡናማዎቹ ማረፊያቸውን ኬሊሎ ሆቴል በማድረግ ነገ ወይም ከነገ በስቲያ መደበኛ ልምምዳቸውን በመከላከያ ኢንጂነሪንግ ሜዳ እንደሚጀምሩ ይጠበቃል። ታዲያ በዚህ የቡድኑ ጉዞ ውስጥ ምክትል አሰልጣኝ ገብረኪዳን ነጋሽ እና የግብጠባቂው አሰልጣኝ ፀጋዘአብ አስገዶም ከቡድኑ ጋር አብረው ሲገኙ ዋና አሰልጣኙ ካሣዬ አራጌ እና ምክትል አሰልጣኙ ዘላለም ከቡድኑ ጋር አብረው እንዳልተጓዙ ታውቋል።
አሰልጣኝ ካሣዬም ሆነ ምክትላቸው ዘላለም ያልሄዱበት ምክንያት ለማጣራት ባደረግነው ጥረት ከፅህፈት ቤት በኩል ምክትል አሰልጣኙ ዘለዓለም ከቡድኑ ጋር እንዳይጓዙ ትዕዛዝ እንደተሰጣቸው ሰምተናል። ምንም እንኳን ነሐሴ 30 ቀን ኮንትራታቸው የሚያልቀው አሰልጣኝ ዘላለም ምን አልባት ክለቡ ውል ለማራዘም ፍቃደኛ ባለመሆኑ ምክንያት ሳይጓዙ እንዳልቀረ ተገምቷል። በዚህ ውሳኔ ደስተኛ ያልሆኑት አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ ዛሬ ከቡድኑ ጋር አብረው ባይጓዙም ነገ ወይም ከነገ በስቲያ ከቡድኑ ጋር እንደሚቀላቀሉ ታውቋል።
በዚህ ጉዳይ የሚኖሩ አዳዲስ ነገሮች ካሉ ተከታትለን የምናቀርብ መሆኑን እንገልፃለን።