ድሬዳዋ ከተማ ተከላካይ አስፈርሟል

አዲስ ጎጆ-ወጪ የሆነው ተጫዋች በዛሬው ዕለት ከባለቤቱ ጋር የፎቶ ፕሮግራም ሲያከናውን ወደ ሌላ የሊጉ ክለብ ያመራበትን ዝውውርም አጠናቋል።

በአሠልጣኝ ዘማርያም ወልደጊዮርጊስ የሚመሩት ድሬዳዋ ከተማዎች በስጋት ካሳለፉት የዘንድሮ የውድድር ዓመት በቀጣይ በተሻለ መልኩ ተጠናክረው ለመምጣት እንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። ሁለቱን የመሐል ተከላካዮች ወደ ሰበታ (በረከት ሳሙኤል) እና ሀዲያ (ፍሬዘር ካሳ) የሸኘው ክለቡም ቀልጣፋውን የመሐል ተከላካይ መሳይ ጳውሎስ የግሉ አድርጓል።

በቅርቡ ትዳር የሚመሰርተው መሳይ በዛሬው ዕለት ለሰርጉ የፎቶ ፕሮግራም ያከናውን ነበር። ከዚህ ፕሮግራም ጎን ለጎን ደግሞ ተጫዋቹ የቀጣይ ዓመት ማረፊያውን የሚወስን ፊርማ ለማኖር ቀጠሮ ይዞ ነበር። ይህንን ተከትሎም ተጫዋቹ ከባለቤቱ ጋር በመሆን ወደ ድሬዳዋ ከተማ የሚያደርገውን ዝውውር በአንድነት ፓርክ እንደፈፀመ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።