ኦኪኪ አፎላቢ ፊርማውን አኑሯል

ድረ-ገፃችን ከሰዓታት በፊት ባስነበበችው መረጃ መሠረት ወደ ፋሲል ከነማ የሚያደርገውን ዝውውር ለማገባደድ አዲስ አበባ የደረሰው አጥቂ በይፋ ፊርማውን አኑሯል።

ግዙፉ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ የዘንድሮውን ግማሽ የውድድር ዘመን ከሲዳማ ቡና ጋር ካሳለፈ በኋላ ወደ አዲስ ክለብ ለማምራት ከሳምንታት በፊት ጀምሮ እንቅስቃሴ ላይ ነበር። የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሻምፒዮን የሆኑት ፋሲል ከነማዎችም ተጫዋቹን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል ከወኪሉ እና ናይጄሪያ ከነበረው ኦኪኪ ጋር ንግግር ሲያደርጉ ነበር። ድርድሮቹ ፍሬ አፍርተውም ተጫዋቹ በዛሬው ዕለት ዝውውሩን ለመጨረስ አዲስ አበባ ደርሷል።

አመሻሽ ላይም የቀድሞ የጅማ አባጅፋር፣ መቐለ 70 እንደርታ እና ሲዳማ ቡና ተጫዋች በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት በመገኘት የአንድ ዓመት ውል ፈርሟል።