ከ17 ዓመት በታች ውድድርን አስመልክቶ ውይይት ተካሂዷል

የፕሪምየር ሊግ እና የክልል ቡድኖችን ባሳተፈ መልኩ ለመጀመርያ ጊዜ የሚዘጋጀው ከ17 ዓመት በታች ውድድርን አስመልክቶ በጁፒተር ሆቴል የተካሄደው የዛሬ ስብሰባ ውሎ…

ከ17 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ከዚህ ቀደም ከ2005 – 2010 ድረስ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን አወዳዳሪነት ሲካሄድ ቆይቶ በተለያዩ ምክንያቶች ለሦስት ዓመት ውድድሩ ተቋርጦ መቆየቱ ይታወቃል። ዳግም ይህን ውድድር በተለየ አቀራረብ የፕሪምየር ሊግ ክለቦችን፣ ሁለት የከተማ አስተዳደሮች እና ክልሎችን ተሳታፊ ባደረገ መልኩ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀውን ውድድር በይፋ ለማስጀመር በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል የዕጣ ማውጣት እና ሥነ ስርዓት እና የደንብ ውይይት ተካሂዷል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ አብዱራዛቅ ሀሰን፣ የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ እና የፌዴሬሽኑ ሜዲካል ዳሬክተር ዶ/ር ሳሙኤል የሸዋስ ታድመዋል።

የመክፈቻ እና የእንኳን ደህና መጣቹሁ ንግግር ያደረጉት አቶ ባህሩ ጥላሁን ይህ ውድድር ለፊፋ ሪፖርት ግብዓት እንዲሆን ታስቦ የተዘጋጀ ውድድር ሳይሆን በትክክል ተተኪ እግርኳስ ተጫዋቾችን ለማፍራት ታስቦ ፌዴሬሽኑ ትኩረት ሰጥቶበት የተዘጋጀ ውድድር መሆኑን ገልፀው ከዚህ ቀደም ይህን ውድድር በተበታተነ ሁኔታ ከክልል ወደ ክልል በመመላለስ የታዳጊዎቹን የትምህርት የጊዜ ሁኔታዎችን የሚጋፋ እንደነበረ እና ይህን አስቀርቶ ትምህርታቸውንም እግርኳሱን በአንድ ላይ ማሰኬድ ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነ ገልጸዋል።

የውድድር ደንቡን አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሰለሞን ገብረሥላሴ የተዘጋጀው ደንብ መነሻ እንደሆነ እና ከጉባኤው ተሳታፊዎች ከሚቀርቡ ግብአቶች በመነሳት ዳብሮ የፀደቀ ቋሚ ደንብ እንደሚኖር በመግቢያ ንግግራቸው ከገለፁ በኃላ በዝርዝር የውድድር ደንቡን አስረድተዋል። አስቀድሞ በደብዳቤ የተገለፀው የውድድሩ ቦታ አዳማ ከተማ እና ባቱ ከተማ እንደሚካሄድ ቢሆንም በተለያዩ አሳማኝ ምክንያቶች በአንድ ከተማ እርሱም በባቱ ከተማ ብቻ እንደሚካሄድ አሳውቀዋል። የተጫዋቾች ምዝገባ፣ የተጫዋቾች ቅያሪ፣ የቅድመ ስብሰባ እና በተለይ አንድ ቡድን ይዞት የመጣውን ተጫዋች ቢያንስ በውድድሩ ላይ በአጠቃላይ 30 ደቂቃ ማጫወት አለበት እና ሌሎች ከደንቡ ጋር የተያያዘ ሰፊ ማብራሪያ ከሰጡ በኃላ ክለቦች እና የክልል እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮች የውድድር መመዝገቢያ ወጪያቸውን የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንደሚሸፍን ገልፀዋል።

በማስከተል በቀረበው ደንብ ዙርያ ከተሳታፊ ክለቦች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበዋል። በዋናነት:-

* የውድድሩ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ ቢቀየር ለምሳሌ ሀዋሳ ቢሆን

* በደንቡ ላይ አንድ ቡድን በአንድ ጨዋታ ዘጠኝ ተጫዋች መቀየር የሚችል እንደሆነ እና እያንዳንዱ ተጫዋች ቢያንስ 30 ደቂቃ መጫወት አለበት የሚለው አስቸጋሪ ነው።

* (የደቡብ ተወካይ) በውድድሩ ላይ እንዳንካፈል በስልክ ጥሪ ብቻ ከላይ ባሉ አመራሮች ትዕዛዝ እየተላለፈበን ስለሆነ ፌዴሬሽኑ ይህን ነገር አውቆ ማሳሰቢያ እንዲሰጥልን በማለት ጠይቀዋል።

ከሻይ እረፍት መልስ አቶ ሰለሞን ለቀረቡት ዋና ዋና ጥያቄዎች ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል። “የመጣው ተጫዋች ተቀምጦ መመለስ የለበትም፤ ሁሉም መሳተፍ አለባቸው። የፌዴሬሽኑ ቴክኒክ ኮሚቴ የእያንዳንዱን ተጫዋች አቅም መገምገም ይፈልጋል። ከዚህ ባሻገር ውድድሩ ተተኪዎችን ከማፍራት አንፃር እንጂ ውጤት ብቻ መታሰብ የለበትም። የውድድር ቦታው ለሁሉም ማዕከል እንዲሆን ታስቦ እና በቂ ዝግጅት የተደረገበት በመሆኑ ባቱ ከተማ ተመራጭ ሆኗል። ብለዋል።

በማስከተል ዶ/ር ሳሙኤል የሸዋስ በውድድሩ ላይ የሚኖረው የMRI ምርመራ ሂደት ምን እንደሚመስል እና የኮቪድ ፕሮቶኮል አስመልክቶ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዴት እንደሚከናወን የተለያዩ ማብራሪያዎችን ሰጥተዋል። ጉባኤው ወደ መጠናቀቂያው ደረሰ ሲባል ተጨማሪ የድግግሞሽ ሀሳቦች በመነሳታቸው ጊዜውን እንዲገፋ ቢያደርገውም በመጨረሻም በአምስት ምድብ የተከፈለ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ተካሂዶ የስብሰባው ፍፃሜ ሆኗል።

የምድብ ድልድሉን ማን ከማን እንዳገናኘ እና በምን መልኩ እንደተካሄደ ረፋድ በነበረው ዘገባችን መግለፃችን ይታወሳል።

ያጋሩ