በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት ከሀምሌ 19 ጀምሮ እየተደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ያለፉ ክለቦችን እያሳወቀ የሚገኝ ሲሆን የምድብ ጨዋታዎችም ሊጠናቀቁ የአንድ ሳምንት መርሐ-ግብር ብቻ ቀርቶታል፡፡
በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስተናጋጅነት ለመጀመሪያ ጊዜ የክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከሀምሌ 19 ጀምሮ በሀዋሳ ከተማ አስተናጋጅነት እየተደረገ ይገኛል፡፡ በሁለት ምድቦች ተከፍሎ በአስር ቡድኖች መካከል በሀዋሳ ግብርና ኮሌጅ ሜዳ ላይ ሲደረግ የሰነበተው ውድድርም ሊጠናቀቅ የአንድ ሳምንት ጨዋታዎች ብቻ የሚቀሩት ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን የ2014 ውድድር ያለፉ ሰባት ክለቦችም ዛሬ በተደረጉ ጨዋታዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡
ዛሬ በተደረገ ጨዋታ ጠዋት 3፡00 የኦሮሚያ ክለብ ሰበታ ከተማ ፔንዳ ክለብን 7ለ0 ያሸነፈ ሲሆን ሰበታ ከተማም የሀዋሳውን ምስራቅ ክፍለ ከተማን 2ለ0 አሸንፏል፡፡ ከሰዓት (8:00) በነበረው መርሐ-ግብርም ጠንካራ ፉክክር በተስተዋለበት ጨዋታ ሱሉልታ ከተማ ከምባታ ዞንን 1ለ0 ሲያሸንፉ የአዲስ አበባው አራዳ ክፍለ ከተማ ከደቡቡ ሀላባ ዞን ጋር ያደረጉት የማሳረጊያ ጨዋታ ያለ ምንም ጎል በአቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡
የዛሬውን ጨዋታ ጨምሮ ቀደም ብሎ በተመዘገቡ ውጤቶች እና የነጥብ ስብስብ መሠረት ቀሪ አንድ ጨዋታ እየቀረ ከምድብ ሀ ስምንት ነጥብ የያዘው አራዳ ክፍለ ከተማ፣ ስድስት ነጥብ የያዘው ሰበታ ከተማ፣ አራት ነጥብ የያዘው ወላይታ ዞን እንዲሁም ሌላኛው አራት ነጥብ የያዘው ሀላባ ከተማ በጊዜያዊ የደረጃ ሰንጠረዥ መሠረት ከአንድ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ በመያዝ ወደ 2014 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ማደጋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን አንድም ጨዋታ ያላሸነፈው ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከምድቡ ሳያልፍ አምስተኛ ሆኖ አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው ሳይሳካለት መቅረቱ ተረጋግጧል፡፡
ከምድብ ለ እኩል ዘጠኝ ነጥብ የያዙት ሱሉልታ ከተማ እና ከምባታ ዞን ወደ ሁለተኛ ዲቪዚዮን ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሲሆን አሰላ ከተማ እና ፔንዳ ክለብ እኩል ሦስት ነጥቦችን የያዙ ሲሆን አለታ ቤዛ ውሀ ደግሞ ምንም ነጥብ መያዝ አልቻለም። በቀጣይ ከዚህ ምድብ ቀሪ ሦስት አላፊ ቡድኖች በመጨረሻው የጨዋታ ውጤት መሠረት የሚለዩም ይሆናል፡፡