የኦሊምፒክ የደረጃ ጨዋታ በኢትዮጵያዊው ዳኛ ይመራል

ነገ ከሰዓት በሜክሲኮ እና ጃፓን መካከል የሚደረገውን የቶኪዮ ኦሊምፒክ የደረጃ ጨዋታ ኢትዮጵያዊው የመሐል ዳኛ ይመራዋል።

በቶኪዮ ከተማ እየተከናወነ የሚገኘው የ2020 የኦሊምፒክ ውድድር በደማቅ ሁኔታ የብዙዎችን ቀልብ በመያዝ ቀጥሏል። በኦሊምፒኩ ከሚደረጉት የተለያዩ የስፖርት አይነቶች መካከል ደግሞ እግርኳስ ይገኝበታል። ቀደም ብሎ ተጀምሮ የነበረው ይህ የስፖርት አይነትም ቅዳሜ ፍፃሜውን እንዲያገኝ መርሐ-ግብር ተይዞለታል።

ቅዳሜ ከሚደረገው ተጠባቂው የስፔን እና ብራዚል የፍፃሜ ጨዋታ በፊት ደግሞ ነገ ከሰዓት በሜክሲኮ እና ጃፓን መካከል የደረጃ ጨዋታ ይደረጋል። ይህንን የደረጃ ጨዋታ ደግሞ በውድድሩ በመሐል እና በአራተኛ ዳኝነት ሲሳተፍ የነበረው ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ባምላክ ተሰማ እንደሚመራው ተመላክቷል። በመድረኩ የደረጃ ጨዋታ የሚመራ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ ዳኛም ይሆናል።

ነሃስ ለማግኘት የሚደረገውን ጨዋታም ባምላክ ከሱዳናዊው የመጀመሪያ ረዳት ዳኛ መሐመድ ኢብራሂም፣ ከኬንያዊው ሁለተኛ ረዳት ዳኛ ጊልበርት ቺሮይት እና ከኒውዝላንዳዊው አራተኛ ዳኛ ማት ኮንገር ጋር በመሆን የሚመራ ይሆናል።

ባምላክ በውድድሩ የስፔን እና አውስትራሊያ እንዲሁም የብራዚል እና ሳውዲ አረቢያ ጨዋታዎች በመሐል ዳኝነት መምራቱ የሚታወስ ነው።