የአሰልጣኝ ብዙአየው ጀምበሩን ውል ያደሰው እና አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ከአንድ ቀን በፊት ያስፈረመው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮኑ ድሬዳዋ ከተማ በዛሬው ዕለት ደግሞ ተጨማሪ አራት አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም የአንድ ነባር ተጫዋችን ውልም አድሷል፡፡
ተከላካይዋ ፀሐይ ኢፋሞ ወደ ቀድሞው ክለቧ ድሬዳዋ ከተማ ከአራት ዓመታት በኃላ በድጋሚ የሚመልሳትን ዝውውር አጠናቃለች፡፡ የቀድሞዋ የሲዳማ ቡና የግራ መስመር የተከላካይ ስፍራ ተጫዋች ያለፉትን አራት የውድድር ጣመታት በሀዋሳ ከተማ ካሳለፈች በኃላ በድጋሚ ወደ ቀድሞው ክለቧ አምርታለች፡፡
አጥቂዋ ቤዛዊት ንጉሤም ወደ ድሬዳዋ አምርታለች፡፡ በ2013 የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዚዮን ተካፋዩ አቃቂ ቃሊቲ ያሳለፈችው ተጫዋቿ በግሏ እጅግ ድንቅ ጊዜ ቢኖራትም ክለቧ ግን ውጤታማ መሆን አልቻለም ነበር፡፡ በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ባሳየችሁ አቋም መነሻነት በሉሲዎቹ ስብስብ ለመካተት የበቃችው ፈጣኗ የመስመር አጥቂ በርካታ ተጫዋቾችን በሌሎች ክለቦች ወደተነጠቀው ድሬዳዋ ተጉዛለች፡፡
በተመሳሳይ ድሬዳዋ ከተማ ከአቃቂ ቃሊቲ አጥቂዋ ሄለን ደሳለኝ፣ ከልደታ ክፍለ ከተማ ደግሞ የግራ መስመር ተከላካይ የሆነችውን ባንቺ ይርጋ ተስፋዬን በይፋ በማስፈረም የአዳዲሶቹን ቁጥር ስምንት አድርሷል፡፡
ክለቡ በአዲስ መልክ ካመጣቸው ተጫዋቾች በተጨማሪ የታታሪዋ የመስመር አጥቂ ታደለች አብርሀምን ውልም ለተጨማሪ ዓመት አራዝሞላታል፡፡