የኢትዮጵያ ቡና ሥራ አመራር ቦርድ ስብሰባ አድርጓል

በወቅታዊ ሁኔታ የኢትዮጵያ ቡና ስራ አመራር ቦርድ ማምሻውን ረጅም ሰዓት የፈጀ ስብሰባ ማድረጋቸው ታውቋል።

ጳጉሜ ወር ላይ በኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ውድድር የሚሳተፈው ኢትዮጵያ ቡና ቅድመ ዝግጅቱን ወደ ቢሾፍቱ በማቅናት በምክትል አሰልጣኙ ገብረኪዳን ነጋሽ አማካኝነት መከወን ከጀመረ ሁለተኛ ቀኑ ላይ ደርሷል። በዚህ የክለቡ ቅድመ ዝግጅት ሒደት ውስጥ ዋና አሰልጣኙ ካሣዬ አራጌ እና ምክትል አሠልጣኙ ዘላለም ፀጋዬ እንዳልተጓዙ መግለፃችን ይታወቃል። ምክንያቱ ደግሞ የአሠልጣኝ ዘላለም ውል ባለመታደሱ እንደሆነና በዚህም ውሳኔ ደስተኛ ባለመሆን አሰልጣኝ ካሣዬ ለክለቡ ፅህፈት ቤት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ገልፀን ነበር።

ዛሬ አመሻሽ ላይ ስብሰባ የተቀመጠው የክለቡ ቦርድ በወቅታዊው ጉዳይ ዙርያ ረጅም ሰዓት የፈጀ ስብሰባ አድርጓል። በስብሰባው ላይ ምን ተነሳ ምንስ የተለየ ውሳኔ ተወሰነ በሚለው ጉዳይ ላይ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው ባይሳካም የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ ለሶከር ኢትዮጵያ ነገ በአጠቃላይ በጉዳይ ዙርያ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ገልፀውልናል። እኛም የክለቡን አቋም ነገ ይዘን የምንቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንገልፃለን።