የዓምናዋ የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ አዘጋጅ ከተማ ጅማ ዳግመኛ ውድድሩን እንዲስተናገድባት ጥያቄ ማቅረቧ ታውቋል።
በ2013 ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ አበባ፣ በጅማ፣ ድሬዳዋ፣ ባህር ዳር እና ሀዋሳ ተካሂዶ መጠናቀቁ ይታወቃል። ባሳለፍነው ዓመት ከነበረው ጥንካሬ እና ድክመት በመነሳት ሊግ ካምፓኒው ቀጣይ የሊጉን ውድድሮች ማዘጋጀት ለሚፈልጉ ክለቦች መስፈርት አውጥቶ በላከው መሠረት 4 ከተሞች ድሬዳዋ ከተማ፣ ባህር ዳር ከተማ፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ ሜዳችን ይታይልን በማለት ደብዳቤ ማስገባታቸውን ሰምተናል።
አሁን ደግሞ አምስተኛ ከተማ በመሆን ጅማ “ዓምና የነበረውን የማሰተናገድ ልምድ ተጠቅመን በ2014 የቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግን በጅማ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ለማዘጋጀት ፍላጎቱ አለን” በማለት በዛሬው ዕለት ለሊግ ካምፓኒው ደብዳቤ ማስገባታቸውን አረጋግጠናል።
ከአክስዮን ማኅበሩ ቦርድ አመራሮች፣ ከፅ/ቤቱ እና ሊግ ኮሚቴው የተቋቋመው ኮሚቴ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ሜዳዎችን በይፋ መገምግም ሊጀምሩ እንደሆነ ታውቋል።