እስካሁን በይፋ እንቅስቃሴ ያልጀመረው የመዲናው ክለብ ጉዳይ…?

👉”የቀጣይ ዓመት ውድድር ዝግጅትን በተመለከተ እስካሁን ከክለቡ የደረሰኝ ምንም አይነት መልዕክት የለም” እስማኤል አቡበከር (አሠልጣኝ)

👉”ዓምናም ዘገያችሁ ስንባል ነበር። ግን የእኛ ክለብ በስልት ነው ሁሉን ነገር የሚያደርገው” ነፃነት ታከለ (ሥራ-አስኪያጅ)

በ2013 የውድድር ዓመት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሁለት ተደልድሎ በ51 ነጥቦች ወደ ዋናው የሀገሪቱ የሊግ እርከን ማደጉን ያረጋገጠው አዲስ አበባ ከተማ እስካሁን እንደሌሎቹ የሊጉ ክለቦች እንቅስቃሴ በይፋ አለመጀመሩ አግራሞትን ፈጥሯል። በአሠልጣኝ እስማኤል አቡበከር እየተመራ የዘንድሮ እቅዱን ያሳካው ክለቡም በአዳዲስ ተጫዋቾች ዝውውር እና ከነባር ተጫዋቾች ውል ማደስ ጋር ስሙ እየተነሳ አለመሆኑ ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል። እርግጥ ሶከር ኢትዮጵያ ባደረገችው ማጣራትም ዋና አሠልጣኙን ጨምሮ በርካታ የቡድኑ ተጫዋቾች እስከ ጥቅምት 30 ውል ያላቸው ቢሆንም የሚቀጥሉት እንዲሁም የሚለቁት ተጫዋቾች እስካሁን እንዳልተለዩ አረጋግጣለች።

እንደገለፅነው ከነባር ተጫዋቾች ውጪ ቡድኑን በአዲስ መልክ ሊቀላቀሉ ከሚችሉ ተጫዋቾች ጋር ምንም አይነት ግንኙነት ያላደረገው ክለቡም አንድ ወር ባስቆጠረው የዝውውር መስኮት ላይ ተሳትፎ ሳያደርግ ዝምታ ውስጥ መክረሙን ተንተርሶ የሚመለከታቸውን አካላት አናግረናል። በቅድሚያም የከፍተኛ ሊጉ ውድድር ሊጠናቀቅ ሦስት ጨዋታዎች እየቀረው ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉት አሠልጣኝ እስማኤል አቡበከርን አግኝተን አናግረናቸዋል። አሠልጣኙም በክለቡ አካሄድ ደስተኛ አለመሆናቸውን ገልፀውልን እስካሁን የትኛውም የክለቡ አመራር አግኝቷቸው እንዳላናገራቸው አስረድተውናል።

“የትኛውም የክለቡ አመራር አግኝቶኝ ከዝውውር ጋር በተያያዘ አላወራኝም። የተጠየኩት ብቸኛ ጥያቄ ያለፈውን የውድድር ዓመት የተመለከተ ሪፖርት እንዳስገባ ብቻ ነው። ሪፖርቱንም እየጨረስኩ ነው። በቅርቡም አስገባለሁ። ከዚህ ውጪ ግን የምትፈልጋቸውን አዳዲስ ተጫዋቾች አናግር ተብዬ አልተነገረኝም። የነባር ተጫዋቾችንም ውል እንዳድስ አልተጠየኩም። እርግጥ የእኔን ጨምሮ የአብዛኞቹ ተጫዋቾች ውል የሚያልቀው ጥቅምት 30 ነው። ይህ ውል ሲጀምር ልክ አይደለም። ሌላ ነገርን የሚጋፋ ውል ነው። የሆነው ሆኖ የቀጣይ ዓመት ውድድር ዝግጅትን በተመለከተ እስካሁን ከክለቡ የደረሰኝ ምንም አይነት መልዕክት የለም።”

በክለቡ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን ቀጣይ ህይወት ያላገናዘበ አካሄድ ነው ክለባችን በአሁኑ ሰዓት እየተከተለ ያለው የሚሉት አሠልጣኝ እስማኤል አብዛኞቹ ተጫዋቾች በተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ እንዳሉ ሳይሸሽጉ ነግረውናል።

“ብዙ ተጫዋቾች እኔ ጋር ይደውላሉ። ሲጀምር ሽልማት አለመሸለማቸው አስከፍቷቸዋል። ሲቀጥል ደግሞ ውላቸው ይታደስ አይታደስ ሳያውቁ እንዲቀመጡ ተደርገዋል። በዚህም ደስተኛ ሳይሆኑ ከክለቡ ለመለያየት ጥያቄ እያቀረቡ ነው። ይሄንን ከሚመለከተው አካል ጋር ያወራሉ። ግን እኔን ሲያማክሩኝ ያለውን የሀገር ነባራዊ ሁኔታ እየነገርኳቸው ታገሱ እያልኳቸው ነው። ስለዚህ ሥራ መስራት ያለበት አካል ሥራውን ቶሎ መስራት አለበት። የዝውውር መስኮቱም ከተከፈተ አንድ ወር አስቆጥሯል። ግን የእኛ ክለብ ምንም እንቅስቃሴ እያደረገ አይገኝም።” ብለውናል።

ሶከር ኢትዮጵያም የአሠልጣኙን፣ የበርካታ ተጫዋቾችን እና ክለቡ አካባቢ ያሉ ግለሰቦችን ሀሳብ እና ጥያቄ ይዛ የክለቡ ሥራ-አስኪያጅ የሆኑትን አቶ ነፃነት ታከለ ጋር አምርታለች። ሥራ-አስኪያጁም በቅድሚያ ክለቡ አሁን ያለበትም ሁኔታ እንዲህ በማለት ገልፀውልናል።

“ዝምታን መርጣችኋል የተባለው ነገር አያስማማም። እንቅስቃሴ ላይ ነን። የክለባችንን አቅም ባገናዘበ መንገድ አዳዲስ ዝውውሮችንም ለማድረግ ሥራ ጀምረናል። አሠልጣኞቻችንም የሚፈልጉትን ተጫዋች እንዲመለምሉ አድርገናል። እነሱ ካመጡ በኋላ ደግሞ በኮሚቴ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ተጠንቶ ዝውውሮቹን የምናደርግ ይሆናል።”

በክለቡ ሥራ-አስኪያጅነት ሁለተኛ ዓመታቸውን ያስቆጠሩት አቶ ነፃነት ቀጥለውም “ዓምናም ዘገያችሁ ስንባል ነበር። ግን የእኛ ክለብ በስልት ነው ሁሉን ነገር የሚያደርገው። ሌሎቹ ክለቦች በፈለጉት መንገድ ሊንቀሳቀሱ ይችላሉ። እኛ ግን ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ነው የምንደገፈው። ዘንድሮም ወደ እንቅስቃሴ ያልገባነው የፀደቀልንን በጀት ስላላወቅን ነው። ባልፀደቀ በጀት ደግሞ ስለተጫዋች ደሞዝ መነጋገር አትችልም። ከበላይ አካላት ጋር በበጀቱ ጉዳይ እየተነጋገርን ነው። ነገርግን በደብዳቤ እስካልደረሰን ድረስ አቅማችንን ማወቅ አንችልም። ይህ ቢሆንም በቃል ደረጃ የምንነጋገራቸውን ታሳቢ በማድረግ አሠልጣኞቻችን ከሚፈልጉት ተጫዋች ጋር እንዲነጋገሩ እያደረግን ነው። ባለፈው ሀገራዊ ምርጫ ነበር። አሁን ደግሞ ሀገራችን ያለችበት ሁኔታ ይታወቃል። እነዚህ ነገሮች ደግሞ ትንሽ ክፍተት እንዲፈጠርብን አድርጎናል።” ይላሉ።

ታዲያ በቀጣይ አካሄዳችሁ ምን ይመስላል? መቼስ ወደ ዝውውሩ ትገባላችሁ ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄም “በፊት ስፖንሰር አይፈቀድም ነበር። አሁን ግን ስፖንሰር እንድናመጣ ፍቃድ አግኝተናል። ይህ ደግሞ በደንብ የሚደጉመን ይሆናል። ቀድሜም እንዳልኩት እጃችንን ያሳጠረው የበጀቱ ጉዳይ ነው። ያለውን ነገር ከበላዮቻችን ጋር ተነጋግረን ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ በይፋ ወደ እንቅስቃሴ እንገባለን። ይህ እንዳለ ሆኖ በአሠልጣኞቻችን አማካኝነትም የሚቀጥሉ እና የማይቀጥሉ ተጫዋቾችን እየለየን ነው። አብዛኞቹ ተጫዋቾች ደግሞ አብረውን ይቀጥላሉ። እንደገለፅኩት ደግሞ ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ተጫዋቾቻችንን እየጠራን የምናናግር ይሆናል።” በማለት ሀሳባቸውን አጠቃለዋል።