ፋሲል ከነማን ከመንግስት ድጎማ በማላቀቅ የራሱ የገቢ ምንጭ እንዲያመነጭ እና የማኅበረሰቡ ተቋም እንዲሆን የሚያስችል ስምምነት በትናንትናው ዕለት ተፈፅሟል።
የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ክለብ የሆነው ፋሲል ከነማ በሜዳም ሆነ ከሜዳ ውጪ ያሉ ሥራዎችን እየሰራ በቀጣይ ዓመታት ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። የሜዳ ላይ ሥራዎቹ እንዳሉ ሆነው ክለቡ ከመንግስት ድጎማ ተላቆ የራሱን የገቢ ምንጭ እንዲያመነጭ እና የማኅበረሰቡ ተቋም እንዲሆን ቅድመ ሥራዎች ሲከወኑ ሰነባብተዋል። የክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፅ እንዳወጣው መረጃ ከሆነ ደግሞ የፋሲል ከነማ የበላይ ጠባቂ እንዲሁም የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ እና የኖቫ ኮኔክሽን ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ጋሻው አበዛ የክለቡን መዋቅር ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሳድግ ስምምነት እንደተፈራረሙ ያመላክታል።
በጎንደር ከተማ ቋራ ሆቴል በተፈፀመው ስምምነት ላይ የፋሲል ከነማ የቦርድ አባላትን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች መገኘታቸው ታውቋል። አቶ ሞላ እና ዶክተር ጋሻው ስምምነቱም ከፈፀሙ በኋላ የክለቡ የበላይ ጠባቂ “የፋሲል ከነማ ስፖርት ክለብ ባለፉት አምስት ዓመታት በሜዳ ውስጥ እና ከሜዳ ውጭ ፈጣን የሚባል እድገት ያስመዘገበ ሲሆን ወደ ሊጉ ካደገበት ዓመት ጀምሮ በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ የፈጠረው መነቃቃት ቀላል የሚባል አይደለም።” የሚል ሀሳባቸውን አስተላልፈዋል። ይህ ቢሆንም ግን የተገኘውን ዕድል ወደ ገንዘብ በመቀየር ክለቡ በሁለት እግሩ እንዲቆም የሚያስችሉ ሥራዎች በሚገባው መጠን እንዳልተሰሩ የገለፁት አቶ ሞላ አሁን ግን ክፍተቱን ለማስተካከል እንቅስቃሴ ላይ መኮኑን አስረድተዋል። አያይዘውም ይህ ስምምነት እንዲፈፀም ጥረት ሲያደርጉ የነበሩ አካላትን አመስግነዋል።
ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ከሌላኛው የክልሉ ክለብ (ባህር ዳር ከተማ) ጋር ተመሳሳይ ሥራ ለመስራት ስምምነት የፈፀሙት ዶክተር ጋሻው አበዛ በበኩላቸው በተደረገው ስምምነት ክለቡን ከፍ ያደርጋሉ የተባሉ ጥናቶች እና ትግበራዎችን ለመፈፀም የተዘጋጁ መሆናቸውን አውስተው በጥናቱም የክለቡን አደረጃጀት ማዘመን፣ የገቢ መጠን ማሳደግ፣ ከመንግስት ጥገኝነት ማላቀቅ እና ሌሎች ሥራዎችን እንደሚከውኑ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ተተግብረው ውጤታማ የሆኑ ሥራዎችን በፋሲል ከነማ ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ ጥረት እንደሚያደርጉ አስረድተዋል።
የኖቫ ኮኔክሽን ድርጅት ሥራ አስኪጅ የሆኑት ዶክተር ጋሻው አበዛ አያይዘው እንደተናገሩት ከሆነ የጥናቱ ዋና ዓላማ የክለቡን ውጫዊ እና ውስጣዊ አደረጃጀቶች መዘርጋት፣ የገቢ መጠኑን ማሳደግ፣ የማኅበረሰብ ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ሥራዎች እንዲሰሩ እንደሚያደርግ እንደሆነ እና ሥራዎቹንም በጥቂት ወራት ወደ መሬት እንደሚወርዱ አመላክተዋል።