👉 “…ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ሲናገሩ…”
👉 “…እኔ ከለመደብኝ ነገር አኳያ ተጫዋቾች መሐል ዘሎ የመግባት ነገር አለኝ”
👉”በአንፃራዊነት ካጫወትኳቸው ጨዋታዎች የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ … ኪሎ ሜትር ሸፍኜ ነበር”
👉 “ፈጣሪ ከፈቀደ በቀጣዩ የኳታር ዓለም ዋንጫ ላይ በመሐል ዳኝነት ማገልገል ህልሜ ነው”
የዓለም ዋንጫ፣ የአፍሪካ ዋንጫ እንዲሁም የአህጉሪቱ ታላላቅ የክለቦች ውድድሮች እና የማጣሪያ ጨዋታዎችን ከዚህ ቀደም የመራው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ ከትናንት በስትያ የተጠናቀቀው የ2020 የኦሊምፒክ የእግርኳስ ውድድር ላይ ግልጋሎት ሰጥቶ ትናንት ከሰዓት ወደ ሀገሩ ተመልሷል። ባምላክ በብራዚል ከ23 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን አሸናፊነት በተጠናቀቀው ውድድር ላይ አሸናፊዋ ብራዚል ከ ሳውዲ አረቢያ፣ ስፔን ከ አውስትራሊያ እንዲሁም ለደረጃ የተደረገውን የአዘጋጇ ጃፓን እና ሜክሲኮን ጨዋታ በዋና ዳኝነት መርቶ ሀገሩን በበጎ ማስጠራቱ ታይቷል። ዳኛው ከሦስቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች በተጨማሪ ደግሞ ሜክሲኮ ከ ብራዚል እና ፈረንሳይ ጋር ያደረገችውን ሁለት ጨዋታዎችንም በአራተኛ ዳኝነት መርቶ ነበር።
የመሐል ዳኛው ትናንት ከሰዓት አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የብሔራዊ ዳኞች ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው እና የሙያ አጋሮቹ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል አድርገውለታል። በቦሌ ከነበረው የእንኳን ደህና መጣህ አቀባበል በተጨማሪም የፌዴሬሽኑ አመራሮች በኦሊምፒክ የእግርኳስ ውድድር በዳኝነቱ ከኢትዮጵያ በብቸኝነት የተጓዘው ባምላክ ወደ ጁፒተር ኢንተርናሽናል ሆቴል ወስደው ግብዣ እንዳደረጉለት ታውቋል። በስፍራውም የኬክ ቆረሳ መርሐ-ግብር እንደተከናወነ ተገልጿል። ሀያ ቀናትን በጃፓን ቶኪዮ ቆይቶ የተመለሰው ባምላክንም ገና ከድካሙ ሳያገግም ሶከር ኢትዮጵያ አግኝታ ቆይታ አድርጋለች።
ቆይታህ እንዴት ነበር ?
እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን ቆይታዬ በአጠቃላይ እጅግ ጥሩ የሚባል ነበር።
የአፍሪካ፣ የዓለም ዋንጫ ትልልቅ ጨዋታዎችን መርተሀል። አሁን ደሞ የኦሊምፒክ ጨዋታዎችን መራህ። አያሌ ኢትዮጵያውያን ታሪክ በሰሩበት ኦሊምፒክ ላይ ጨዋታዎችን መምራት ምን ስሜት ይፈጥራል?
ከባድ ስሜት ነው። ከአበበ ቢቂላ አሁን እስካሸነፈው ሰለሞን ባረጋ ድረስ የኢትዮጵያ ባንዲራ በትልቁ የዓለም የስፖርት መድረክ በኦሊምፒክ ከፍ እንዲል ያደረጉ ዕንቁዎች ካሉባት ሀገር ነው የሄድኩት። በእኔ ዕድሜ እንባቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ከዐይን ላይ ብቻ የሚወጣ የማይመስል ዕንባን ለሀገራቸው ሲያነቡ ተመልክቻለሁ። እውነት ለመናገር እነዛን ጊዜያቶች በማየት እንደ አንድ የእግርኳስ ዳኛ እንዲህ ዓይነት ቦታ ላይ መገኘትን አልም ነበር። እግዚአብሔር ታላቅ ነው ይህንን ዕድል በዚህ ጊዜ ሰጠኝ። የሄድኩትም በእግዚአብሔር ነው ማለት ይቻላል። በኮሮና ምክንያት ይህ ውድድር ሊሰረዝ ነበር። ከዚህ ባለፈ በአንዳንድ የልምምድ ቦታዎች የኢትዮጵያን ባንዲራ በአትሌቲክስ ማስጠራት ማለት ምን ዓይነት ድካም፣ ልፋት እና ጥረት እንደሚጠይቅ ታላላቅ አትሌቶችን ሳገኝ ማየት ችያለሁ። ለመሄድ ጥቂት ቀን ሲቀረኝ የኦሊምፒክ ኮሚቴው ዕድል ሰጥቶኝ እነሱ የሚሰሩበት የልምምድ አካባቢ ለመሥራት ዕድል አግኝቻለሁ። አትሌቶች ምን ያህል ለሀገራቸው እንደሚሠሩ ስመለከት እንዲሁም በውድድሩ ቦታ በተለያየ የስፖርት ዓይነት እና በተለያየ ሙያ ሀገራቸውን ለማስጠራት ደፋ ቀና ሲሉ ሳይ ዕድሉ በህይወቴ አንዴ የሚገኝ ዓይነት መሆኑን እንድገነዘብ አድርጎኛል። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ የሆነ መነሳሳት ፈጥሮብኛል። ያለኝን የመጨረሻ ነገር እንድሰጥም አድርጎኛል።
በአንፃራዊነት ከመራሀቸው አጠቃላይ አምስት ጨዋታዎች ከበድ ያለህ የቱ ነበር?
ከግምገማዎቹ አንፃር ስታየው የመጀመሪያዎቹን ጨዋታዎች ፍፁም ጥሩ በሆነ ውጤት ነው ማጫወት የቻልኩት። ምክንያቱም ያለኝን ነገር ሁሉ ለማሳየት ሞክሬያለሁ። ከዛ በኋላ የብራዚል እና የሳውዲ አረቢያ ጨዋታ በአንፃራዊነት ከሦስቱ ጨዋታዎች ከበድ ያለ ነው ማለት ይቻላል። የሳውዲ አረቢያ ብሔራዊ ቡድን በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ይጫወታል ተብሎ አልታሰበም ነበር። የብራዚል ብሔራዊ ቡድንን ጨዋታ አሸንፎ ለቀጣዩ ዙር ማለፍ ነበረባቸው። ስለዚህ ሲጀምር ባልተጠበቀ ሁኔታ ሳውዲ አረቢያዎች ቀድሞ ጎልም በማስቆጠር ጨዋታውን ከባድ አድርገውት ነበር። የቡድኑ የአጨዋወት ፍልስፍና እና በጨዋታው የነበረው አቀራረብም ጨዋታውን ከባድ አድርጎት ነበር ፤ ከመቆጣጠር አኳያ። ግን እግዚያብሔር ይመስገን ጨዋታው በጥሩ ሁኔታ ነበር የተጠናቀቀው።
በቆየህባቸው 20 ቀናት ያጋጠመህ ገጠመኝ ይኖር ይሆን?
በውድድሩ ከኮቪድ-19 አኳያ በየቀኑ ሳምፕል መስጠት ነበረብን። መውጣት መግባትም አይቻልም ነበር ፤ ከሆቴል ወደ ልምምድ ቦታ ከልምምድ ቦታ ወደ ሆቴል ብቻ ነበር እንቅስቃሴ። የሀገርህን ውድድር እንኳን ማየት አይፈቀድልክም። የኮቪድ ፕሮቶኮሉ ፍፁም የተለየ ነበር ማለት ይቻላል። ከሌሎች ከተሳተፍኩባቸው ውድድሮች አንፃር በጣም ጥብቅ ነበር። የመጀመሪያውን ጨዋታ ያጫወትኩት ራቅ ወዳለ ከተማ ሄጄ ነበር። ወደዛ በፕሌን ስንሄድ እንኳን ከሌላ ሰው ጋር መገናኘት የተከለከለ ነበር። ቁጥጥሩ በጣም ከፍተኛ ነበር። የገጠመኝ ጠንከር ያለው ነገር ይህ ነው። ከዚህ ውጪ ልምምዶችን መሥራት የግድ ይጠይቃል። የሚሰጡም ፈተናዎች ነበሩ። ቪ ኤ አር (VAR) ለመጀመሪያ ጊዜ ነው በኦሊምፒክ የተተገበረው። ከእሱ ጋር መጣመር ያስፈልግ ነበር። እኛ ያው ይህንን ዕድል የምናገኘው በአፍሪካ ደረጃ እሱንም በግማሽ ፍፃሜ እና ፍፃሜ ላይ ማጫወት ስንችል ብቻ ነበር። እሱን ቶሎ ለመልመድ ትንሽ ጊዜ ፈጅቶብኝ ነበር። እግዚአብሔር ታላቅ ነው፤ ምንም ዓይነት VAR review አላጋጠመኝም። እኔም ሆንኩ ከእኔ ጋር የሰሩ ረዳት ዳኞች የሰጠናቸው ውሳኔዎች በቪዲዮ ተደግፈው ማረጋገጫ ስላገኙ እንደፈራነው አልሆነም እና መልካም ነበር ማለት ይቻላል።
በመሐል ዳኝነት እና በአራተኛ ዳኝነት በመራሀቸው አምስት ጨዋታዎች ከውሳኔዎችህ ውስጥ ባይሆን ኖሮ ወይም እንዲህ ባልወስን ብለህ ለራስህ ጥያቄ የፈጠረብህ ይኖር ይሆን?
እግርኳስ ዳኝነት ላይ አጫውተህ ስትወጣ በዚህም በዚያም የተለያዩ ሀሳቦች ሊሰነዘሩ ይችላሉ። አስታውሰህ ከሆነ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ በፓርላማ ሲናገሩ ‘ሁለት ቡድኖች ሲጫወቱ ለእኔ እንደዚህ ይሁን ለእኔ እንደዚህ ይሁን ቢሉ በVAR ይታይ’ ነው የሚባለው ነበር ያሉት። የእግርኳስ ዳኛ ስለሆንኩ ከመሰጡኝ ንግግራቸው ውስጥ አንዱ ይሄ ነው። እና ባጫወትናቸው ጨዋታዎች ላይ ቪ ኤ አር የነበረ በመሆኑ ውሳኔዎቻችንን በአግባቡ ከማየት አካያ እዛው ውጤቱን ስለምናገኝ እንዲህ ባደረኩ ኖሮ የሚል ነገር አላጋጠመኝም ዕድለኛ ሆኜ። ምናልባት ልል የምችለው ከአጨዋወት ዘይቤ ጋር በተገናኘ በመጨረሻው ጨዋታ (ጃፓን ከሜክሲኮ) ላይ ራሴን ነጥዬ መሮጥ እንዳለብኝ አስቤ አድርጌው ነበር። አሁን አሁን ሳስበው አንዳንድ ቅፅበቶች ላይ ቀረብ ብል እላለሁ። ከዚህ ውጪ ማካለል የሚገቡኝ ቦታዎች ላይ ያልሸፈንኩባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ ፤ በውሳኔ ደረጃ ችግር ባይኖርባቸውም።
ከሁሉም ጨዋታዎች በኋላ ግምገማዎች ይደረጋሉ። እነዚህ ግምገማዎች የሚደረጉት በፊፋ መምህራኖች በቪዲዮ ነው። ግምገማዎቹ ሲደረጉ ስታይልን ፣ ማኔጅመንትን የተመለከቱ የተነገሩኝ ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ያህል የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ስታጫውት አብዛኛውን ነገር በቢጫ እና ቀይ ካርድ ልትቆጣጠር አትችልም። አንዳንድ ጊዜ በመገላገል እና በመነጋገር የሚደረጉ ነገሮች አሉ። እና እኔ ከለመደብኝ ነገር አኳያ ተጫዋቾች መሀል ዘሎ የመግባት ነገር አለኝ። እንደነዚህ ዓይነት ነገሮች ግን ትልልቅ በሆኑ ውድድሮች ላይ ብዙም አይመከሩም። የሚደረጉበት ቦታ አለ የማይደረጉበት ቦታ አለ ፤ ገደብ አላቸው። ይህ የሚደረግባቸውን ቦታዎች እንድለይ ትምህርት ሰጥተውኛል።
በመሐል ዳኝነት ካጫወትካቸው ሦስት ጨዋታዎች ረጅም ኪሎ ሜትር ያካለልክበት ጨዋታ የቱ ነበር? ስንትስ ኪሎ ሜትር ሸፈንክ?
እንደየ ጨዋታዎቹ ባህሪያት ይለያያሉ። የቡድኖቹም የጨዋታ አይነት ይህ ጉዳይ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል። በአንፃራዊነት ካጫወትኳቸው ጨዋታዎች የመጀመሪያው ጨዋታ ላይ 12.4 ኪሎ ሜትር ሸፍኜ ነበር። እንደምታውቀው ዳኝነት መንቀሳቀስ ይፈልጋል። ኳስ ባለችበት ቦታ ላይ ወዲያው ተገኝተህ ቅፅበቶቹን ካላየህ የሚሰሩት ጥፋቶች በጣም ፕሮፌሽናል ስለሆኑ ልትሸወድ ትችላለህ። አንዳንዶቹን ንክኪዎች እንደውም በዐይን ለመለየት እራሱ የሚያስቸግሩ ናቸው። ስለዚህም ቅፅበቶቹን ቦታው ላይ በመገኘት ማየት ስለሚጠይቅ መታተር አለብህ።
በዚህ ውድድር ላይ ምን የተለየ ትምህርት አገኘህ?
በጣም ብዙ ነገሮች ተምሬያለሁ። አንደኛ ይህ ውድድር በዓለም ደረጃ ትልቅ ስም እና ዝና ካላቸው ተጫዋቾች ጋር እንድገናኝ አስችሎኛል። እነዚህ ትላልቅ ተጫዋቾችም ምን እንደሚፈልጉ በደንብ እንዳውቅ አድርጎኛል። ከእነርሱም ጋር በምን አይነት መንገድ መግባባት እንዳለብኝ እንዳውቅ አስችሎኛል። ይሄን ዕድል በሌላ መድረክ ያላገኘሁም ነበር። ስለዚህ ውድድሩ የዓለማችን ምርጥ ተጫዋቾች በምን አይነት መንገድ እንደሚጫወቱ እንዳይ አድርጎኛል። እነርሱንም እንዴት አድርጌ መቆጣጠር እንዳለብኝ እንድገነዘብ አድርጎኛል። ይህ ትልቅ ልምድ ነው። ከዚህ ውጪ ቪ ኤ አርን በትልቅ ውድድሮች እንዴት ማጫወት እንዳለብኝ ረድቶኛል። ከቴክኖሎጂውም ጋር ቶሎ እንድላመድ ስጥር ነበር። ይህም ተሳክቶልኝ ትልቅ ዕውቀት ሸምቼበታለሁ። በፊት በአትሌቲክሱ ልብ የሚነኩ ነገሮችን የሀገር ባንዲራ ሲውለበለብ አያለሁ። ይህንንም ሳይ በውድድሩ ለመካፈል አልም ነበር። አሁን ጊዜው ደርሶ በውድድሩ ተካፍዬ ያንን ስሜት አይቼዋለሁ። ተጋርቼዋለሁም። ይህንን ስሜት በሌላ መድረክ አላገኘውም ነበር።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ትናንት አዲስ አበባ ስትደርስ አቀባበል አድርገውልሀል። ጠብቀከው ነበር? ስሜቱስ እንዴት ነበር?
ይህንን አልጠበቁም ነበር። የእግርኳስ ዳኝነት የጋራ ሥራ ነው። እኔ እዚህ ደረጃ እንድደርስ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። ለፍቶብኛል ማለት እችላለሁ። ፌዴሬሽኑ ብቻ ሳይሆን ክለቦች እና ተመልካቾችም ትልቅ አስተዋጽኦ አድርገውልኛል። የሆነው ሆኖ በትላልቅ መድረኮች ላይ ሀገርን መወከል ታላቅ ክብር እንዳለው ትናንት ታዝቤያለሁ። ከፕሬዝዳንቱ ጀምሮ የጽሕፈት ቤት ኃላፊው፣ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የሙያ አጋሮቼ ቦሌ ድረስ መተው አቀባበል አድርገውልኛል። ይህ ለእኔ ትልቅ ክብር ነው። ተግባሩ እኔን ብቻ ሳይሆን ወጣት ዳኞችም በዚህ ደረጃ እንዲሰሩ የሚያበረታ ነው። በአጠቃላይ ለእኔ የተደረገው ነገር ከጠበኩት በላይ ነበር። በድርጊቱም ኮርቻለሁ።
በርካታ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የብሔራዊ ቡድን እና የክለብ ውድድሮችን እስካሁን መርተካል። አሁንስ ይቀረኛል ወይም ማሳካት አለብኝ የምትለው ነገር አለህ?
ኦሊምፒክ የስፖርት ውድድሮች የመጨረሻ ውድድር ነው። በዚህም ውድድር በዋና ዳኝነት ነው የተካፈልኩት። እንደምታውቀው በዓለም ዋንጫ ውድድር ኢትዮጵያዊ ዳኛ ሲዳኝ ከስዩም ታረቀኝ ቀጥሎ ሊዲያ ታፈሰ ነች ያለችው። እኔ በሩሲያው የ2018 ዓለም ዋንጫ ሀገሬን የወከልኩት በአራተኛ ዳኝነት ብቻ ነው። የዋና ዳኝነት ሚና አላገኘሁም ነበር። በዚህም ውስጤ ከፍተኛ የሆነ ቁጭት እና ህልም አድሮብኛል። ስለዚህ በቀጣይ ፈጣሪ ከፈቀደ በቀጣዩ የኳታር ዓለም ዋንጫ ላይ በመሐል ዳኝነት ማገልገል ነው። ከዚህ ውጪ በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች የመምራት ዕድሉ ብቻ ነበረኝ። በቀጣይ ግን ይህንን የአህጉሪቱ ውድድር የፍፃሜ ጨዋታ ብመራ ምኞቴ ነው። በተጨማሪም የኢትዮጵያን እግርኳስ ዳኝነት እዚህ ካደረሱት የሙያ አጋሮቼ ጋር ሆኜ ዳኝነቱን ከፍ ለማድረግ ነው ራዕዬ።
በመጨረሻ…?
እኔ እዚህ ደረጃ የደረስኩት በብዙ ሰዎች ውጤት ነው። ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን፣ ለሀርመን ሀንሰን የሪሰርች ተቋም፣ ለኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ለካፒታል ሆቴል ባለቤት አቶ የማነህ፣ ለአስተማሪዎቼ፣ ለጓደኞቼ፣ የተለያዩ ውድድሮችን አብረውኝ ለዳኙ ረዳት ዳኞች፣ ለክለቦች እና ለኢትዮጵያ የስፖርት ቤተሰብ ምስጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ። ዳኛ ስትሆን ትሳሳታለህ። ቪ ኤ አር ቢኖርም ልትሳሳት ትችላለህ። የጠቀስኳቸው አካላት ይህንን ሁሉ ችለው እዚህ ስላደረሱኝም በጣም አመሰግናለሁ። ሶከር ኢትዮጵያን ጨምሮ ሚዲያዎችም ከስህተታችን እንድንታረም ስለምታደርጉን ላመሰግናችሁ እወዳለሁ።