ከሲዳማ ቡና ጋር የተለያየው ተጫዋች ወደ አዳማ አቅንቷል

ለአምስት ዓመታት ግልጋሎት ከሰጠበት ክለብ ጋር የተለያየው የአማካይ መስመር ተጫዋቹ አዳማ ከተማን መቀላቀሉ ተረጋግጧል።

ከሀዋሳ ከተማ የተስፋ ቡድን ተገኝቶ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ዮሴፍ ዩሐንስ ወደ ሲዳማ ቡና በማምራት ያለፉትን አምስት ዓመታት ማገልገሉ አይዘነጋም። ተጫዋቹ ከሲዳማ ጋር እስከ ቀጣይ ዓመት የሚያቆየው ውል ቢኖረውም በትናንትናው ዕለት በስምምነት መለያየቱን ዘግበን ነበር።

ዮሴፍ በትናንትናው ዕለት ራሱን ነፃ ካደረገ በኋላ ዛሬ ወደ አዳማ በማቅናት ከቀናት በፊት የጀመረውን ድርድር አገባዶ ለአዳማ ከተማ ለመጫወት ፊርማውን ማኖሩን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ያጋሩ