በዝውውሩ እየተካፈለ የሚገኘው ወላይታ ድቻ በዛሬው ዕለት አንድ አዲስ ተከላካይ ሲያስፈርም የነባር ተጫዋቹን ውልም አድሷል፡፡
በረከት ወልደዮሐንስ ወደ ወላይታ ድቻ አምርቷል፡፡ የእግር ኳስ ህይወቱን በትውልድ ከተማው ሆሳዕና የጀመረው በረከት ወደ አርባምንጭ ከተማ 2011 ተጉዞ ከተጫወተበት ጊዜ ውጪ አብዛኛዎቹን የእግር ኳስ ህይወቱን በሀድያ አሳልፏል፡፡ ተጫዋቹ የተጠናቀቀውን የውድድር ዓመት በሀድያ ሆሳዕና እስከ አጋማሹ ድረስ ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ጋር በተፈጠረ ያለመግባባት መጫወት ያልቻለ ሲሆን አሰልጣኙ ክለቡን ከለቀቁ በኃላ ግን በመጨረሻዎቹ ጨዋታዎች ተሰልፎ ተጫውቷል፡፡ በአሳዳጊ ክለቡ የነበረው ውል መጠናቀቁን ተከትሎ ወላይታ ድቻን በሁለት ዓመት ውል በዛሬው ዕለት ተቀላቅሏል፡፡
ከአዲስ ፈራሚው ባለፈ ወላይታ ድቻ የነባሩን ወጣት ግብ ጠባቂ ቢኒያም ገነቱን ውል ለተጨማሪ ዓመት አድሷል፡፡ በወላይታ ድቻ ከ17 እና ከ20 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ ተጫውቶ ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኃላ ያለፉትን ሦስት ዓመታት ምንም እንኳን የመሰለፍ ዕድልን ማግኘት ባይችልም የቡድኑ አባል ሆኖ የቆ ሲሆን ለቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት ውሉ ተራዝሞለታል፡፡