በሀዋሳ ከተማ እየተደረገ ባለው የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና ከሰዓት በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ወደ አንደኛ ሊግ ያደጉ ተጨማሪ አራት ቡድኖች ተለይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና በሀዋሳ ከተማ ከሐምሌ 18 ጀምሮ በአርባ ስድስት ክለቦች መካከል እየተደረገ ዘልቆ ወደ መገባደጃው ደርሷል፡፡ የምድብ ጨዋታዎች ተጠናቀው በዛሬው ዕለት ወደ አስራ ስድስት ውስጥ የገቡ ቡድኖች ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ረፋድ በተደረጉ ጨዋታዎች ዱከም ከተማ፣ ካማሺ ከተማ፣ ቦሌ ክፍለከተማ እና ቡሳ ከተማ ተጋጣሚዎቻቸውን በመርታት ወደ አንደኛ ሊግ ማለፋቸውን በዘገባችን ጠቁመን ነበር፡፡
ከሰዓት ጨዋታዎች ቀጥለው ተጨማሪ አራት ቡድኖች በተደረጉ አራት ጨዋታዎች ተለይተው ታውቀዋል፡፡ ሀዋሳ ሰው ሰራሽ ሜዳ ላይ ከሰዓት ሁለት ጨዋታ ተከውኖ 7፡00 ሲል ሁለቱ የጋምቤላ ቡድኖች ኑዌር ዞን ከ ጋምቤላ አብይ አካዳሚ ተገናኝተው መደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 2ለ2 ተለያይተው በተሰጠው የመለያ ምት ጋምቤላ አብይ አካዳሚ 5ለ4 በሆነ ውጤት ማደጉን አረጋግጧል፡፡ በመቀጠል በዚሁ ሜዳ 9፡00 ላይ ቫርኔሮ ወረዳ 13 ከ ወንዶ ገነት ተገናኝተው 0ለ0 ወጥተው በተሰጠ መለያ ምት 3ለ1 የአዲስ አበባው ተወካይ ቫርኔሮ ወረዳ 13 አሸንፎ የ2014 የአንደኛ ሊግ ተሳትፎውን አረጋግጧል፡፡
በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲም በተመሳሳይ ሁለት ጨዋታዎች ተደርገዋል፡፡ 7፡00 ላይ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ከሱማሌ ክልል በብቸኝነት የተወዳደረው ካራማራ ጋር ያደረጉት ጨዋታ 1ለ1 አቻ ተለያይተው በተሰጠው የመለያ ምት 4ለ3 በሆነ ድል የሀዋሳው ምስራቅ ክፍለ ከተማ አዳጊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ 9፡00 ላይ ዱራሜ ከተማን ከሊሙገነት ከተማ አገናኝቶ ከደቡብን የተወዳደረው ዱራሜ 1-0 አሸንፎ ወደ አንደኛ ሊግ አላፊ መሆኑን አረጋግጧል፡፡
ዛሬ በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች ስምንት ቡድኖች ማለትም ዱከም ከተማ፣ ቡሳ ከተማ፣ ካማሺ ከተማ፣ ቦሌ ክፍለከተማ፣ ዱራሜ ከተማ፣ ቫርኔሮ ወረዳ 13፣ ጋምቤላ አብይ አካዳሚ እና ምስራቅ ክፍለከተማ ወደ 2014 የአንደኛ ሊግ የመሳታፊያ ትኬትን ቆርጠዋል፡፡ በአንፃሩ በዛሬው ዕለት የተሸነፉት ስምንት ቡድኖች በሚያደርጉት የአርስ በእርስ ጨዋታ ቀሪ አራት ቡድኖች ወደ አንደኛ ሊጉ ለማደግ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡