የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጋጣሚ ስብስቧን አሳውቃለች

በ2022 የሴቶች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ አቻውን የሚገጥመው የሩዋንዳ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል።

በ2022 በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች የዓለም ከ20 ዓመት በታች ዋንጫ ውድድር ላይ የሚሳተፉ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎችን ማድረግ ጀምረዋል። በአህጉራችን አፍሪካም የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ተደርገው ሲገባደዱ የሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታዎች ደግሞ በመስከረም ወር መደረግ ይጀምራሉ። በአሠልጣኝ ፍሬው ወልደገብርኤል የሚመራው የኢትዮጵያ ሴቶች ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንም በሁለተኛ ዙር የማጣሪያ ጨዋታ የሩዋንዳ እና የደቡብ ሱዳንን አሸናፊ ለመግጠም መርሐ-ግብር ተይዞለት ነበር። ይህ ቢሆንም ደቡብ ሱዳን ከውድድሩ ራሷን ማግለሏን ተከትሎ በሁለተኛ ዙር ማጣሪያ የኢትዮጵያ እና የሩዋንዳ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች እንደሚጫወቱ ታውቋል።

2008 ላይ ከጀርመን የሌቭል ቢ ላይሰንስ በማግኘት የመጀመሪያዋ እንስት ፕሮፌሽናል አሠልጣኝ በመሆን በሩዋንዳ የእግርኳስ ታሪክ በተመዘገበችው ናይናዋሙንቱ የሚመራው ብሔራዊ ቡድኑም ትናንት አመሻሽ በመስከረም ወር አጋማሽ ከኢትዮጵያ አቻው ጋር ላለበት ጨዋታ ለተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል። ጥሪ ከተደረገላቸው 39 ተጫዋቾች ውስጥም አራት የግብ ዘቦች፣ ዘጠኝ ተከላካዮች፣ 13 አማካዮች እና 13 አጥቂዎች መካተታቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ እና ሩዋንዳ የመጀመሪያ ጨዋታ ከመስከረም 13-15 ሩዋንዳ ላይ ሲደረግ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከመስከረም 27-29 ኢትዮጵያ ላይ እንደሚደረግ የወጣው መርሐ-ግብር ያመላክታል። እስካሁን በይፋ እንቅስቃሴ ያልጀመረው የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድንም በቅርቡ ለተጫዋቾች ጥሪ በማድረስ ዝግጅት እንደሚጀምር ይጠበቃል።