አሠልጣኝ ካሣዬ እና ኢትዮጵያ ቡና ከስምምነት የደረሱ ይመስላል

ከተጫዋቾቹ ጋር ወደ ቢሾፍቱ ሳይጓዝ የቀረው አሠልጣኝ ካሣዬ ክለቡ ያስቀመጠውን አቅጣጫ በጊዜያዊነት መቀበሉ ታውቋል።

በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ ያገባደደው ኢትዮጵያ ቡና ከፊቱ ላለበት የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅቱን ለማድረግ በሳምንቱ መጀመሪያ ቀናት (ማክሰኞ) ወደ ቢሾፍቱ ማምራቱ ይታወቃል። የቡድኑ ተጫዋቾች እና አንደኛው ምክትል አሠልጣኝ ገብረኪዳን ነጋሽ በታሰበው ቀን ወደ ቢሾፍቱ ቢያመሩም ዋና አሠልጣኙ ካሣዬ አራጌ የምክትል አሠልጣኙ ዘላለም ፀጋዬ ውል አለመታደስ አስከፍቶት ወደ ስፍራው ሳያቀና ቀርቶ ነበር። ይህንን ተከትሎም አሠልጣኝ ካሣዬ ክለቡ የረዳቱን ውል እንዲያድስለት ደብዳቤ አስገብቶ ምላሽ ሲጠባበቅ እንደነበር ይታወቃል።

የአሠልጣኙን ጥያቄ ከሁለት ቀን በፊት (ሀሙስ ምሽት) ሲመለከት የነበረው የክለቡ የሥራ አመራር ቦርድም ሥራ እንዳይበደል አሠልጣኙ ቡድኑን እያዘጋጀ ጥያቄውን እንዲያቀርብ አቅጣጫ አስቀምጦ ነበር። ይህ ክለቡ የሰጠውን ሀሳብ ተቀብሎም አሠልጣኝ ካሣዬ አራጌ በዛሬው ዕለት ቡድኑ ወዳረፈበት ቢሾፍቱ ከተማ ማቅናት ከተጫዋቾቹ ጋር ትውውቅ ሰላምታ እንደተለዋወጠ እንዳደረገ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አሰልጣኝ ካሣዬ ወደ ስፍራው ያቅና እንጂ ምክትል አሰልጣኙ በቀናት ውስጥ ውሉ ታድሶለት ከቡድኑ ጋር የማይቀላቀል ከሆነ ዳግመኛ ጉዳዩ ወደ ሌላ ምዕራፍ እንዳይሻገር ተሰግቷል።