ዋልያዎቹ ነገ ወደ አዳማ እንደሚያቀኑ ይጠበቃል

በትናንትናው ዕለት ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ነገ ወደ አዳማ ከተማ እንደሚጓዝ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ቡድኑ ከጋና እና ዚምባብዌ ጋር ለሚያደርጋቸው ሁለት የዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርበው ነበር። ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች ትናንት ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የካፍ የልዕቀት ማዕከል እየተገኙ ሪፖርት እንዲያደርጉ እና እንዲሰባሰቡም ተመላክቶ ነበር። ሶከር ኢትዮጵያ ከምንጮቿ አግኝታ ረፋድ ላይ እንዳስነበበችው ዘገባም በግል ምክንያት አማካዩ ሀይደር ሸረፋ እና አጥቂው ሙጂብ ቃሲም ከስብስቡ ውጪ የሆኑ ሲሆን ቀሪዎቹ 26 ተጫዋቾች ግን ትናንት እና ዛሬ ተጠቃለው በማዕከሉ እንደተገኙ ታውቋል።

ትናንት እና ዛሬ የተሰበሰቡት ተጫዋቾችም ዛሬ አመሻሽ 11 ሰዓት በጊዜያዊነት ማረፊያ ባደረጉበት ማዕከል የኮቪድ-19 ምርመራ እንደተደረገላቸው ተጠቁሟል። ምርመራ የተደረገላቸው 26 ተጫዋቾች፣ አራት ዋና እና ረዳት አሠልጣኞች እንዲሁም አንድ የቪዲዮ አናሊስት፣ የህክምና ባለሙያ እና ትጥቅ ያዥ በአጠቃላይ 33 ልዑካን ነገ ረፋድ የኮቪድ ውጤታቸውን ከሰሙ በኋላ ዝግጅታቸውን በቋሚነት ወደሚያደርጉበት አዳማ ከተማ እንደሚያቀኑም ይጠበቃል። ቡድኑም ከነገ ከሰዓት ጀምሮ ልምምድ እንደሚጀምር ተሰምቷል።