ሀድያ ሆሳዕና በማለዳው ሁለት አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል፡፡
ኢያሱ ታምሩ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ያመራው አንደኛው ተጫዋች ነው፡፡ በአማካይ ስፍራ ፣ በመስመር አጥቂነት እና በመስመር ተከላካይነት ቦታ መሰለፍ የሚችለው ይህ ሁለገብ ተጫዋች ሀላባ ከተማን 2007 ክረምት ላይ ከለቀቀ በኃላ ያለፉትን ስድስት የውድድር ዓመታት በኢትዮጵያ ቡና በመጫወት አሳልፏል፡፡ በኢትዮጵያ ቡና ቤት ከተሰጠው የመጫወት ሚና ባሻገር በሁለተኛ አምበልነት ጭምር ክለቡን ያገለገለው ተጫዋቹ ቡናማዎቹን በመልቀቅ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ማምራቱ ዕርግጥ ሆኗል፡፡
በትናንትናው ዕለት አንድ ዓመት የውል ዕድሜ ከባህር ዳር ከተማ ጋር እየቀረው ከክለቡ ጋር እንደተለያየ ዘግበን የነበረው አማካዩ ሳምሶን ጥላሁን መዳረሻውን ሀድያ ሆሳዕና አድርጓል፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ ከተስፋ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት ከቻለ በኃላ በደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና እንዲሁም ከተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ጀምሮ ደግሞ ወደ ባህርዳር አምርቶ በክለቡ እስከ ተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ድረስ ቆይታን አድርጓል፡፡ በባህርዳር ከተማ በቀጣዩ የ2014 የውድድር ዓመት የሚያጫውተው ቀሪ ውል የነበረው ተጫዋቹ ከሰሞኑ የስምምነት ድርድር ከጣና ሞገደኞቹ ቤት ካደረገ በኃላ በመለያየት በሁለት ዓመት ኮንትራት ወደ ሀድያ ሆሳዕና አምርቷል፡፡