የሊጉ አክሲዮን ማኅበር ዛሬ ወደ ሀዋሳ አቅንቷል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የበላይ የሆነው አክሲዮን ማኅበሩ ዛሬ ወደ ሀዋሳ አቅንቶ ከዩኒቨርስቲው አመራሮች ጋር ውይይት አድርጓል።

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ የመዝጊያ አምስት የጨዋታ ሳምንታትን አስተናግዶ የነበረው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም የቀጣይ ዓመት ውድድርንም ዳግም ለማስተናገድ ጥያቄ ማቅረቡን ከቀናት በፊት መዘገባችን ይታወሳል። የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበርም የቀጣይ ዓመት ውድድርን ለማስተናገድ ጥያቄ ያቀረቡ ስታዲየሞችን ከዛሬ ጀምሮ መመልከት የጀመረ ሲሆን በቅድሚያም የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየምን ምልከታ እናዳደረገ ሶከር ኢትዮጵያ ተገንዝባለች።

የአክስዮን ማኅበሩ ሥራ አስኪያጅን ጨምሮ ከጽሕፈት ቤት እና ከሊግ ኮሚቴው የተወጣቱት አራት ግለሰቦች ዛሬ ረፋድ የዩኒቨርስቲውን ስታዲየም አሁናዊ ሁኔታ ከመገምገማቸው ጎን ለጎን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል። በዚህም ከአዲስ አበባ የተጓዘው ኮሚቴ ከሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር በራሶ ኡላ፣ ከዩኒቨርስቲው ጽሕፈት ቤት ኃላፊ እንዲሁም ከሲዳማ ክልል የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬው አሬራ ጋር ተወያይተዋል። በውይይቱም ሜዳው ከዚህ በተሻለ እንክብካቤ ተደርጎለት እንዲስተካከል፣ በቀጣይ ዓመት የምሽት ጨዋታዎች ስለሚኖሩ ፓውዛዎች እንዲተከሉ እንዲሁም የመብራት አቅርቦት ቢቋረጥ እንደ አማራጭነት እንዲያገለግል ጄኔሬተር እንዲዘጋጅ ሀሳብ መነሳታቸውን ለማወቅ ችለናል።

ውድድሩን ለማስተናገድ ጥያቄ ያቀረቡ ስታዲየሞችን መመልከት የሚቀጥለው ኮሚቴውም በነገው ዕለት የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ስታዲየምን ለመመልከት ቀጠሮ መያዙን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።