ተጨማሪ አራት ክለቦች ወደ አንደኛ ሊግ አድገዋል

ከክልል ክለቦች ሻምፒዮና ወደ 2014 አንደኛ ሊግ ያለፉ ክለቦች በዛሬው ዕለት ሙሉ ለሙሉ ተለይተው ሲታወቁ የሩብ ፍፃሜ መርሀ ግብርም ተከናውኗል፡፡

የኢትዮጵያ ክልል ክለቦች ሻምፒዮና የ2013 የውድድር ዓመት በሀዋሳ ከሐምሌ 18 ጀምሮ በአርባ ስድስት ክለቦች መካከል እየተደረገ ሰንብቶ ከቀናቶች በፊት ስምንት ክለቦች ወደ ኢትዮጵያ አንደኛ ሊግ መግባታቸውን ያረጋገጡ ሲሆን ተሸናፊ የነበሩ ቀሪዎቹ ስምንት ክለቦች ደግሞ በዛሬው ዕለት እርስ በእርስ ተጫውተው አሸናፊ የሆኑ አራት ክለቦች ቀድመው ያለፉ አራት ክለቦችን ተከትሎ የ2014 የአንደኛ ሊግ የተሳትፎ ትኬታቸውን ቆርጠዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሜዳ 2፡00 ሲል ሊሙገነት ከተማን ከምኅረት ያገናኘው ቀዳሚ መርሀግብር ተጠቃሽ ነው፡፡ ጨዋታው በመደበኛ ሰአቱ 1ለ1 ተጠናቆ በተሰጠው የመለያ ምት የኦሮሚያው ክለብ ሊሙገነት ከተማ 4ለ3 አሸንፎ ማደጉን ሲያረጋግጥ በመቀጠል አዲስ ቅዳም እና ካራማራን ባገናኘው ጨዋታ ደግሞ የአማራ ክልሉ አዲስ ቅዳም አንድ ለምንም በሆነ ውጤት ድል አድርጓል፡፡ በዚሁ ሜዳ ሦስተኛው ጨዋታ ቦዲቲ ከተማ ወንዶ ገነት ከተማን 3ለ0 ሲያሸንፍ የጋምቤላው ኑዌር ዞን በበኩሉ ቡሬ ዳሞትን 3ለ1 በማሸነፍ ወደ 2014 አንደኛ ሊግ አድገዋል፡፡

ወደ አንደኛ ሊጉ ለማደግ ከተደረገው ጨዋታ ባሻገር ወደ ግማሽ ፍፃሜ የሚያልፉ ክለቦችን የሚለየው ጨዋታም በሀዋሳ አርቴፊሻል ሜዳ ላይ ተደርጓል፡፡ ዱራሜ ከተማ ቦሌ ክፍለ ከተማን 2ለ1፣ የሀዋሳው ምስራቅ ክፍለ ከተማ ካማሺ ዞንን 3ለ0፣ ቡሳ ከተማ ቫርኔሮ ወረዳን 2ለ1 የመጨረሻ መርሀግብር የሆነው የጋምቤላው አብይ አካዳሚ እና ዱከም ከተማ ጨዋታ በአንፃሩ በጋምብላው አብይ አካዳሚ 3ለ2 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ተሸጋግረዋል፡፡

ወደ 2014 አንደኛ ሊግ ያደጉ ያደጉ 12 ክለቦች

ቦሌ ክፍለ ከተማ ፣ ዱራሜ ከተማ ፣ ካማሺ ከተማ ፣ ምስራቅ ክፍለከተማ ፣ ቡሳ ከተማ ፣ ቫርኔሮ ወረዳ 13 ፣ ዱከም ከተማ ፣ ጋምቤላ አብይ አካዳሚ ፣ ሊሙገነት ከተማ ፣ አዲስ ቅዳም ከተማ ፣ ቦዲቲ ከተማ ፣ ኑዌር ዞን


ያጋሩ