በትናንትናው ዕለት የቀጣይ ዓመት የሊጉ ጨዋታዎችን ለማስተናገድ ጥያቄ ያቀረቡ ስታዲየሞችን ምልከታ ማድረግ የጀመረው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር ዛሬ ወደ አዳማ አምርቶ ግምገማ አድርጓል።
የ2014 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን ለማስተናገድ ጥያቄ ካቀረቡ ስታዲየሞች መካከል ቀዳሚው የሀዋሳ ዩኒቨርስቲ በትናንትናው ዕለት በሊጉ የበላይ አክሲዮን ማኅበሩ በተቋቋመው ኮሚቴ ምልከታ እንደተደረገበት እና ማሻሻያ በሚያስፈግላቸው ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይት እንደተደረገ ዘግበን ነበር። የሀዋሳ ቆይታውን ትናንት አገባዶ የተመለሰው ኮሚቴውም ዛሬ ወደ አዳማ ከተማ ማቅናቱን ሰምተናል።
የቀጣይ ዓመት የሊጉ ውድድርን ለማስተናገድ ጥያቄ ካቀረቡ ስታዲየሞች መካከል አንዱ የሆነው እና የዩኒቨርስቲ ውድድሮችን ከዚህ ቀደም የማስተናገድ ልምድ ያለው የአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩንቨርስቲ ስታዲየም የሀገሪቱን ከፍተኛ የሊግ እርከን ውድድር የማስተናገድ አቅም እንዳለው ተገምግሟል። እንደ አክሲዮን ማኅበሩ መረጃ ከሆን ኮሚቴው ስታዲየሙን ከመመልከቱ ጎን ለጎን የዩኒቨርስቲውን ፕሬዝዳንት ዶ/ር ለሚ ጉታ፣ ምክትል ፕሬዝዳንቶች ዶ/ር ተሾመ አብዱ እና ዶ/ር ሀብታሙ በሪ ጋርም ተገናኝተው እንደተወያየ ያመላክታል። ከዩኒቨርስቲው አመራሮች በተጨማሪ የአዳማ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት አቶ ሟታ አብደላ እና ሥራ አስኪያጁ አንበሴ መገርሳ ከመለማመጃ ሜዳዎች እና ከሆቴሎች አንፃር ሌሎች የሚያስፈልጉ ቦታዎችን ማስጎብኘታቸውም ታውቋል።
በቀጣይ ደግሞ ስታዲየሞችን ለመመልከት እና ለመገምገም የተቋቋመው ኮሚቴ ከቀናት በኋላ ወደ ባህር ዳር እና ድሬዳዋ እንደሚያመራ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።