ዐፄዎቹ ለዝግጅት ባህር ዳር ገብተዋል

ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር የሚወክለው ፋሲል ከነማ ለውድድሩ ዝግጅት ባህር ዳር ገብቷል።

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ የሆነው ፋሲል ከነማ ለአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር እና ለቀጣይ ዓመት የሊጉ ፍልሚያ ራሱን ለማጠናከር ከአንድ ወር በላይ ባስቆጠረው የዝውውር መስኮት ገበያ ላይ በመውጣት ተጫዋቾችን ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ ራሱን ሲያጠናክር ሰንብቷል። በዝውውሩም የኦኪኪ አፎላቢ፣ አብዱልከሪም መሐመድ እና አስቻለው ታመነን የግሉ ያደረገው ክለቡ በጿጉሜ ወር ላለበት የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የመጀመሪያ ዙር የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ዝግጅቱን ለማድረግ በትናንትናው ዕለት በባህር ዳር ከተማ ተሰባስቧል።

በባህር ዳር አዲስ አምባ ሆቴል መቀመጫውን ያደረገው ክለቡም እንዲሰባሰቡ ጥሪ ካቀረበላቸው ተጫዋቾች አስራ አምስቱ ይህንን ዘገባ እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ መገኘታቸው ታውቋል። ከአስራ አምስቱ ተጫዋቾች ውጪ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ሀብታሙ ተከስተ፣ ይሁን እንዳሻው፣ ሱራፌል ዳኛቸው እና ሽመክት ጉግሳ ግን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ለሀገራዊ ግዳጅ ጥሪ ስለቀረበላቸው ስብስቡን እንዳልተቀላቀሉ ለማወቅ ተችሏል።

ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ ስብስቡን ካልተቀላቀሉት ስድስት ተጫዋቾች በተጨማሪም አዲሱ የቡድኑ ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ እና የመሐል ተከላካዩ ከድር ኩሊባሊ ከሥራ ፍቃድ እና ማለቅ ከሚገባቸው የወረቀት ጉዳዮች ጋር በተገናኘ እስካሁን ባህር ዳር እንዳልደረሱ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በሁለት ቀናት ውስጥ ግን ተጫዋቾቹ የቀራቸውን የወረቀት ጉዳዮች አገባደው ቡድኑን እንደሚቀላቀሉም ተጠቁሟል።

በትናንትናው ዕለት የተሰባሰበው የክለቡ ልዑክም ዛሬ የአጠቃላይ የህክምና ምርመራ እንደሚደረግለት ተነግሯል። ከዛሬው የህክምና ምርመራ በኋላ ደግሞ ቡድኑ ከነገ ጀምሮ መደበኛ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም የመለማመጃ ሜዳ እንደሚያደርግ ተገልጿል። ምናልባት በዚህ ሳምንት በተጠቀሰው ሜዳ ልምምዱ ተጀምሮ በቀጣይ ግን በዋናው ስታዲየም አልያም በዩኒቨርሲቲው ሜዳ ልምምዶች ሊቀጥሉ ይችላሉም ተብሏል።

በጊዜያዊነት በዋና አሠልጣኙ በተያዘው እቅድ መሠረት በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈሉ በአጠቃላይ የ33 ቀናት የዝግጅት ጊዜ ያለው ክለቡም የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ለማግኘት እንቅስቃሴ ላይ መሆኑንም ድረ-ገፃችን ተገንዝባለች።