ሳላሀዲን ሰዒድ ወደ አዲስ ክለብ አምርቷል

በአጠቃላይ ለስምንት ዓመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው አጥቂ ወደ አዲስ ክለብ ያመራበትን ዝውውር አጠናቋል።

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ከተለያየ በኋላ ቀጣይ የእግርኳስ ሕይወቱን በየትኛው ክለብ ይመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ሳላሀዲን ሰዒድ ማረፊያውን ጅማ አባ ጅፋር አድርጓል። ተጫዋቹ ዛሬ መስቀል ፍላወር በሚገኘው ሞስ ሆቴል በመገኘት ከጅማ ጋር ውል መፈራረሙንም ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

በ1990ዎቹ መጨረሻ በሙገር ሲሚንቶ የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረው ሳላሀዲን በ2000 ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ በማምራት የእግርኳስ ህይወቱ ከፍታ ላይ መድረስ ችሏል። በመቀጠል ወደ ግብፁ ዋዲ ዴግላ እና በውሰት ወደ እህት ክለቡ የቤልጅየሙ ሊርስ ክለብ አምርቶ የተጫወተው ሳሃሀዲን ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ዋንጫ እንድትመለስ ከፍተኛ ሚና ከተጫወተ በኋላ በግብፁ ታላቅ ክለብ አል አህሊ እና አልጄርያው ኤምሲ አልጀር ተጫውቶ አሳልፏል። 2008 አጋማሽ ላይ ዳግም ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ለቅዱስ ጊዮርጊስ በመፈረም እስከ ተጠናቀቀው ዓመት ድረስ የተጫወተ ሲሆን አሁን ደግሞ ወደ ጅማ አባጅፋር ማምራቱ ተረጋግጧል።

ሳላዲን ወደ ጅማ አባ ጅፋር ማምራቱን ከተትሎ ከአስርት ዓመታት በኃላ ዳግም የወላጅ አባቱን እግር በመከተል የመጫወት እድል የሚያገኝ ሲሆን የሳላሀዲን አባት ከዚህ ቀደም ለጅማ አባ ቡና፣ በጅማ መምህራን ኮሌጅ ስር ጥበብ ፋና ለሚባል ቡድን አስራ አንድ ቁጥር ማልያ ለብሰው መጫወታቸው ይታወሳል።

ያጋሩ