ሰበታ ከተማ የመስመር ተጫዋቹን ውል አድሷል

የነባር ተጫዋቾችን ውል እያደሰ አዳዲስ ተጫዋቾችንም ወደ ስብስቡ እየቀላቀለ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከደቂቃዎች በፊት የመስመር ተጫዋቹን ቆይታ ማራዘሙ ታውቋል።

አሠልጣኝ ዘላለም ሽፈራውን ከቀጠሩ በኋላ በዝውውር ገበያው ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች በርካታ ነባር ተጫዋቾቻቸውን ቢያጡም የጥቂቶቹን ውል በማደስ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም የፍፁም ገብረማርያም፣ ዱሬሳ ሹቢሳ እና ናትናኤል ጋንቹላን ውል አድሶ የነበረው ክለቡም ከደቂቃዎች በፊት የመስመር ተጫዋቹን ኢብራሂም ከድር ውል ለተጨማሪ ዓመት ማራዘሙ ታውቋል።

ጅማ አባ ጅፋር ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ አባል የነበረው እና የሊጉን ዋንጫ 2010 ላይ ከክለቡ ጋር አንስቶ የነበረው ኢብራሂም ቻምፒዮን ከሆነበት ዓመት ማግስት ወደ ሰበታ ከተማ ማምራቱ ይታወሳል። የመስመር አጥቂ፣ የመስመር ተከላካይ እና አማካይ ሆኖ መጫወት የሚችለው ተጫዋቹም ያለፉትን ሦስት ዓመታት በሰበታ ግልጋሎት የሰጠ ሲሆን አሁንም ለተጨማሪ ዓመት በክለቡ ለመቆየት ፊርማ ማኖሩ ተረጋግጧል።

ያጋሩ