ዋልያው አዳማ ገብቷል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬ ከሰዓት አዳማ በመግባት ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅቱን ጀምሯል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ላሉበት የጋና እና ዚምባብዌ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረቡ ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ባሳለፍነው ዓርብ ለተጫዋቾች ጥሪ ካቀረበ በኋላ እሁድ ዕለት በካፍ የልዕቀት ማዕከል መሰባሰብ ጀምሮ ነበር። ከትናንት በስትያ እና ትናንት አጠቃሎ በማዕከሉ የገባው ልዑኩም (በግል ጉዳይ ፍቃድ ከተሰጣቸው ሀይደር ሸረፋ እና ሙጂብ ቃሲም ውጪ) ትናንት አመሻሽ 11 ሰዓት የኮቪድ-19 ምርመራ በማድረግ በቋሚነት ዝግጅቱን ወደሚያደርግበት አዳማ ለማምራት ሲዘጋጅ ነበር።

የብሔራዊ ቡድኑ ተጫዋቾች ሲ ኤም ሲ አካባቢ በሚገኘው የልዕቀት ማዕከል አዳራቸውን ካደረጉ በኋላ ማለዳ 1 ሰዓት ላይ በአካል ብቃት አሠልጣኙ ዶ/ር ዘሩ በቀለ የፊትነስ ቴስት እንደተደረገላቸው ለማወቅ ተችሏል። የአካል ብቃት አሠልጣኙ በማለዳ ቴስቱን ከወሰዱ በኋላ ተጫዋቾቹ እረፍት ያደረጉ ሲሆን ከምሳ ሰዓት በኋላም መደበኛ ልምምዳቸውን ወደሚያደርጉበት አዳማ ከተማ አምርተዋል። አስር ሰዓት አካባቢ የደረሰው ቡድኑም በኤክስኪውቲቭ ሆቴል ማረፊያውን እንዳደረገ ተጠቁሟል።

ለሰዓት ከተጠጋውን ጉዞ በኋላ ለትንሽ ደቂቀ እረፍት ያደረጉት ተጫዋቾቹም 11 ሰዓት ገደማ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ቀለል ያለ ልምምድ አድርጓል። ከነገ ጀምሮ ደግሞ ማለዳ (ከ1:00 እስከ 2:30) እና አመሻሽ (ከ10:30 እስከ 12:00) በቀን ሁለት ጊዜ ልምምድ መስራት እንደሚቀጥልም ታውቋል።

ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና አጥቂው አቡበከር ናስር እና ፍፁም ዓለም ከቡድኑ ጋር ወደ አዳማ እንዳልተጓዙ ተረጋግጧል። ድረ-ገፃችን ከደቂቃዎች በፊት እንዳስነበበችው አቡበከር በግል ጉዳይ ምክንያት ከአሠልጣኙ ፍቃድ ጠይቆ መሆኑ እና በሁለት ቀን ውስጥ እንደሚቀላቀል ሲታወቅ የአማካዩ ፍፁም ምክንያት ግን በግልፅ አልተገለፀም። ሁለቱ ተጫዋቾች ከቡድኑ ጋር ባይኖሩም ከደቂቃዎች በፊት እንደዘገብነው አሠልጣኝ ውበቱ ለቸርነት ጉግሳ እና ለበዛብህ መለዮ እንደ አዲስ ጥሪ አቅርበው ወደ አዳማ እንዳቀኑም ሰምተናል።

ያጋሩ