አቡበከር ናስር ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ስብስብ ጋር ወደ አዳማ አላቀናም

የወቅቱ የኢትዮጵያ እግርኳስ ቁንጮ የሆነው አቡበከር ናስር ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ ወደ አዳማ ሲያቀና አብሮ እንዳልተጓዘ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የ2013 የኢትዮጵያ ቤትኪንግ ፕሪምየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ እና የሴካፋ ውድድር ኮከብ ተጫዋች በመሆን ያጠናቀቀው አቡበከር ናስር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከፊቱ ላሉበት ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች (ጋና እና ዚምባብዌ) ጥሪ ቀርቦለት እንደነበር ይታወቃል። ተጫዋቹ በትናንትናው ዕለት በካፍ የልህቀት ማዕከል ተገኝቶ የኮቪድ-19 ምርመራ ማድረጉም ታውቆ ነበር።

አቡበከር ከቡድን አጋሮቹ ጋር ዛሬ ወደ አዳማ እንደሚያመራ ቢጠበቅም በግል ጉዳይ ምክንያት ከብሔራዊ ቡድኑ አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ፍቃድ ወስዶ ወደ ስፍራው እንዳላቀና ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በዚህም በዛሬው የቡድኑ የመጀመርያ ልምምድ ላይ ያልተገኘ ሲሆን የግል ጉዳዩን ነገ በማገባደድም በሁለት ቀን ውስጥ ወደ አዳማ በማቅናት ስብስቡን እንደሚቀላቀል ተመላክቷል።

ያጋሩ