ሁለት ጊዜ የተራዘመው የቻምፒየንስ ሊግ ማጣሪያ ውድድር የሚጀምርበት ቀን ተገልጿል

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሚሳተፍበት የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የምስራቅ አፍሪካ ዞን የማጣሪያ ውድድር ለሁለት ጊዜ ከተገፋ በኋላ የሚካሄድበት ቀን ታውቋል።

በቀጣይ ዓመት በግብፅ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የመጀመሪያው የሴቶች የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአህጉሩ የሊግ አሸናፊ ክለቦች በስድስት ዞን ተከፋፍለው የማጣሪያ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ መገለፁ ይታወቃል። በሴካፋ ዞን የሚገኙ የቀጠናው የሊግ አሸናፊዎችም በሦስት ምድብ ተከፋፍለው በቅድሚያ ከሐምሌ 10 ጀምሮ የማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ተገልፆ የነበረ ቢሆንም ባልታወቀ ምክንያት ቀኑ ተገፍቶ ነበር።

በቀጣይ ደግሞ የምድብ ድልድሉ ወጥቶ ውድድሩ ከነሃሴ 1 ጀምሮ ይደረጋል ቢባልም አስተናጋጇ ኬንያ “የማስተናግደው ሌላ ውድድር አለብኝ” ብላ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዝሞ ነበር። አሁን የኬንያ ብዙሃን መገናኛዎች እንደሚዘግቡት ከሆነ ደግሞ ይህ ውድድር ከነሃሴ 22 (ኦገስት 28) ጀምሮ እስከ ጿጉሜ 4 (ሴፕቴምበር 9) እንደሚደረግ ቀጠሮ መያዙን ያመላክታሉ። በቅርቡም እንደ አዲስ የምድብ ድልድሉ በሁለት ምድብ ተደርጎ እንደሚሰራ ተጠቁሟል።

በውድድሩ ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ በቢሾፍቱ ከተማ ዝግጅቱን ሲያደርግ የነበረው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከቀናት በፊት ተጫዋቾቹን መበተኑ ይታወሳል። አሁን ግን ዋና አሠልጣኙ ብርሃኑ ግዛው ተጫዋቾቹን ዳግም በመሰብሰብ በቀሪ ቀናት ዝግጅታቸውን እንደሚቀጥሉ ይታሰባል።