ዐፄዎቹ ልምምድ ሲጀምሩ ሁለቱ ተጫዋቾችም ቡድኑን ተቀላቅለዋል

ለአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ባህር ዳር የከተመው ፋሲል ከነማ ልምምድ ሲጀምር ሁለቱ ተጫዋቾችም ስብስቡን ተቀላቅለዋል።

በአሠልጣኝ ሥዩም ከበደ የሚመሩት የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ፋሲል ከነማዎች ከዓመቱ መገባደጃ ቀናት ጀምሮ ላለባቸው የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት ለማድረግ ከትናንት በስትያ በባህር ዳር ከተማ እንደተሰባሰቡ ዘግበን ነበር። ለብሔራዊ ቡድን ግዳጅ አዳማ ከሚገኙት ተጫዋቾቻቸው ውጪ አዲስ እና ነባር ተጫዋቾቻቸውን ያገኙት ዐፄዎቹም በትናንትናወ ዕለት አጠቃላይ የህክምና ምርመራ ለተጫዋቾቻቸው እንዳደረጉ ታውቋል።

ከትናንቱ አጠቃላይ ምርመራ በኋላ ደግሞ ቡድኑ በዛሬው ዕለት በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም በሚገኘው የመለማመጃ ሜዳ ዝግጅቱን እንደጀመረ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል። በሦስት ምዕራፎች የተከፋፈለው የቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ዛሬ ጠዋት ሲጀምርም አሠልጣኝ ሥዩም ቀለል ያሉ ሥራዎችን እንዳሰሩ ተገልጿል።

ከቡድኑ ጋር በተያያዘ ዜና በትናንቱ ዘገባች ከወረቀት ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ስብስቡን እንዳልተቀላቀሉ የገለፅናቸው ኦኪኪ አፎላቢ እና ከድር ኩሊባሊ ምሽት ላይ ወደ ባህር ዳር እንዳቀኑ ሰምተናል። ተጫዋቾቹ አጋሮቻቸውን በአዲስ አምባ ሆቴል ካገኙ በኋላም በዛሬው የመጀመሪያ ልምምድ ላይ እንደተገኙ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

ያጋሩ