የአንጋፋው ስታዲየም እድሳት አሁናዊ ሁኔታ

ከወር በፊት የእድሳት ሥራው የተጀመረለት የአዲስ አበባ ስታዲየም አሁን ያለበት ወቅታዊ ሁኔታ ምን ይመስላል

በርካታ ውስጥ እና አሁጉራዊ ውድድሮችን ያስተናገደው አንጋፋው የአዲስ አበባ ስታዲየም የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጎለት በሁለት ምዕራፍ የተከፈለ ሥራዎችን ለመሥራት የስፖርት ኮሚሽን በ39,644,748.93 ብር ፍሬንድስ ኢንጅነሪንግ ኃ የተ የግል ኩባንያ ጋር ስምምነት ማድረጉ ይታወሳል።

በመጀመርያው ምዕራፍ የሜዳው ፣ የመልበሻና የመታጠቢያ ክፍሎች፣ የተመልካች መፀዳጃ እና የኤሌክትሪክ እና የሳኒተሪ ስራዎችን ሲያካትት በሁለተኛው ምዕራፍ የሚዲያ ክፍሎች፣ የክብር ቲሪቡን መቀመጫ ፣ የወንበር ገጠማ ፣እና ሌሎች የስታዲየሙ ክፍሎችን የማደስ እና ለአገልግሎት ምቹ የማድረግ ሥራን ያካተተ ነው።

ብዙም ሳይቆይ ሥራውን የወሰደው የኮንክራስሽን ድርጅት የመጀመርያ ምዕራፍ ሥራውን ጀምሮ ሜዳውን የማረስ እና አንዳንድ ክፍሎችን ሥራ መጀመሩን ይታወቃል። ወደ ውስጥ ዘልቆ ሥራው በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መረጃ ለመስጠት በስፍራው ያሉ አካላት ፍቃደኛ ባይሆኑም ሶከር ኢትዮጵያም በራሷ ጥረት ግንባታው በምን ሂደት ላይ እንደሚገኝ ዛሬ ምልከታ አድርጋ ነበር።

ሜዳው የመጀመርያ አካባቢ ከተደረገለት ቁፋሮ ውጭ ሥራው በዛው ቆሞ የሚገኝ ሲሆን እንዳውም ለበዓላት ማከናወኛ ቀይ አፈር ተበትኖበት ይገኛል። ሥራው የቆመበትን ምክንያት ስናጣራ ከክረምት ወራቱ ጋር በተያያዘ በተፈለገው መልኩ ለማከናወን አስቸጋሪ እንዳደረገው ሰምተናል። ሌላኛው የስታዲየሙ ክፍል የሆነው መልበሻ ቤት እና መታጠቢያ ቤቱ ግን በጥሩ ሁኔታ እየተከናወኑ ለመታዘብ ችለናል።

በ2014 አጋማሽ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ በሚጠበቀው በዚህ የግንባታ ሂደት ውስጥ አሁን ያለውን መጓተት ሲታይ በተባለበት ጊዜ ለማጠናቀቅ ስለመቻሉ አጠያያቂ ነው። ይህን ተከትሎም የቤትኪንግ ፕሪሚየር ሊግ በ2014 የውድድር ዘመን የሀገሪቱ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ ከተማ ምንም ዓይነት ውድድር ላይካሄድበት ይሆን የሚል ጥያቄ ያስነሳል።

ያጋሩ