ሱፐር ስፖርት ለሊጉ ክለቦች ስልጠና ሊሰጥ ነው

ለአምስት ዓመታት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የምስል መብት የገዛው ሱፐር ስፖርት ከደቡብ አፍሪካ በሚያመጣቸው ባለሙያዎች ለክለቦች ስልጠና ሊሰጥ ነው።

ግዙፉ የቴሌቪዥን ተቋም ሱፐር ስፖርት የኢትዮጵያ ከፍተኛ የሊግ እርከን (ፕሪምየር ሊግ) ውድድርን ከ2013 ጀምሮ ለአምስት ዓመታት በቀጥታ ለማስተላለፍ የቴሌቪዥን መብቱን በጨረታ ተወዳድሮ መግዛቱ ይታወቃል። ከምስል መብቱ በተጨማሪ የስያሜ መብቱንም የግሉ አድርጎ ለቤትኪንግ አሳልፎ የሰጠው ተቋሙ የፕሪምየር ሊጉን ገፅታ (ብራንድ) ከፍ የሚያደርጉ ሥራዎችን ለመከወን በእንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ሶከር ኢትዮጵያ አሁን ባገኘችው መረጃም ሱፐር ስፖርት በፕሪምየር ሊጉ ከሚሳተፉ አስራ ስድስቱ ክለቦች የተወጣጡ የክለብ ፕሬዝዳንቶች እና ሥራ-አስኪያጆችን ብራንዲንግን፣ የክለብ አስተዳደርን እና የተጫዋቾች ዝውውርን በተመለከተ ስልጠና ለመስጠት ቀጠሮ ይዟል። ከደቡብ አፍሪካ በሚመጡ ባለሙያዎች የሚሰጠው ስልጠና ሀሙስ እና ዓርብ በሀያት ሪጀንሲ ሆቴል እንደሚከናወንም ለማወቅ ተችሏል።

ያጋሩ