ዋልያዎቹ ልምምድ መስራታቸውን ቀጥለዋል

ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች በትናንትናው ዕለት ልምምድ መስራት የጀመረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዛሬም በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ልምምዱን አከናውኗል።

ከያዝነው ወር መጨረሻ ጀምሮ ከጋና እና ዚምባብዌ ጋር ላሉት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች የተሰባሰበው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ እየተመራ ዝግጅት ማድረጉን ቀጥሏል። የቡድኑ አሠልጣኝ ባሳለፍነወ ዓርብ ለ28 ተጫዋቾች ጥሪ ቢያቀርቡም የኮቪድ-19 ምርመራ አድርገው በቋሚነት ዝግጅት ወደሚያደርጉበት አዳማ ከተማ ያመሩት በቅድሚያ ጥሪ ከደረሳቸው ውስጥ ሀያ አራቱ ብቻ ነበሩ። ሀይደር ሸረፋ እና ሙጂብ ቃሲም በቋሚነት አቡበከር ናስር እና ፍፁም ዓለሙ ግን ፍቃድ በመጠየቃቸው ምክንያት ወደ አዳማ ባይጓዙም ቸርነት ጉግሳ እና በዛብህ መለዮ እንደ አዲስ ጥሪ ቀርቦላቸው በትናንትናው ዕለት ስብስቡን መቀላቀላቸውን ዘግበን ነበር።

በአዳማ ኤክስኪዩቲቭ ሆቴል ማረፊያውን ያደረገው ቡድኑም ዛሬ ማለዳ እና አመሻሽ የሁለተኛ ቀን ልምምዱን አከናውኗል። ማለዳ ከ1 ሰዓት እስከ 2:30 ድረስ አመሻሽ ላይ ደግሞ ከ11:10 እስከ 12:25 ድረስ ልምምድ ተሰርቷል። በተለይ ሶከር ኢትዮጵያ አዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም ተገኝታ ሁለተኛውን የዕለቱ የልምምድ መርሐ-ግብር የተመለከተች ሲሆን በመርሐ-ግብሩም አሠልጣኙ በአመዛኙ ከኳስ ጋር የተገናኙ ሥራዎችን ሲያሰሩ ነበር።

በስታዲየሙ በነበረ ሌላ ውድድር በ30 ደቂቃዎች ተገፍቶ የተጀመረው የብሔራዊ ቡድኑ የአመሻሽ ልምምድ በቅድሚያ አምስት በአንድ ተኮኖ መሐል ባልገባ ሲሰራ ነበር። ተጫዋቾቹ ለአምስት ተከፋፍለው ይህንን ከኳስ ጋር የማላቀቅ እንቅስቃሴ ከከወኑ በኋላ ዋናው ሜዳ ሲለቀቅላቸው ደግሞ ወደ ሜዳው በመግባት በተደራጀ ሁኔታ አራት ቡድን ሰርተው በሁለት ተከፍለው የሩብ ሜዳ ጨዋታ ሲጫወቱ ታይቷል። ቴክኒካዊ ብቃታቸውን እና ከኳስ ጋር ያላቸውን መስተጋብር ለማሳደግ የሚጠቅም የሚመስለው ልምምድ ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች በሁለት ምዕራፎች ከተከናወነ በኋላ ግን የቡድኑ የምሽት ልምምድ ፍፃሜውን አግኝቷል።

ቡድኑ ወደ ዋናው ሜዳ ገብቶ ልምምዱን ሲቀጥል የመሐል ሜዳ ተጫዋቹ ሀብታሙ ተከስተ ጉዳት አስተናግዶ ነበር። ተጫዋቹ ከሌላ ተጫዋች ጋር ተጋጭቶ ከተጎዳ በኋላ ልምምዱን መጨረስ ከብዶት አቋርጦ ሲወጣም አይተናል። የቡድኑ የህክምና ባለሙያ ተጫዋቹን ሲያክሙ ቢታይም ሀብታሙ ተመልሶ ወደ ልምምዱ መግባት ሳይችል ቀርቶ በዛው ከሜዳ ወጥቷል።

የግብ ጠባቂዎች አሠልጣኝ ደሳለኝ ወልደጊዮርጊስ በበኩላቸው አራቱን የግብ ዘቦች ለብቻቸው በመነጠል ቀለል ያሉ ነገርግን ኳስን መሠረት ያደረጉ እንቅስቃሴዎችን ሲያሰሩ አይተናል። በዋናነት ደግሞ ግብ ጠባቂዎቹ በእግራቸው ኳስ እንዲጫወቱ የሚያደርግ ሥራ ሲያሰሩ አስተውለናል።

በትናንትናው ዘገባችን እንደጠቆምነው አቡበከር ናስር እና ፍፁም ዓለሙ በዛሬው የልምምድ መርሐ-ግብር ላይም በተሰጣቸው ፍቃድ ምክንያት አልተገኙም። ተጫዋቾቹ የተሰጣቸው ፍቃድ እየተገባደደ ስለሚገኝም በቅርብ ቀናት ስብስቡን እንደሚቀላቀሉ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደ ዛሬው ሁሉ በቀጣዮቹ ቀናትም በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን እየሰራ እንደሚቀጥል ተጠቁሟል።ያጋሩ