ጅቡቲ እና ኤርትራ ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያቸውን በአዲስ አበባ ያከናውናሉ

በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ለሚከናወነው የ2022 ከ20 ዓመት በታች የሴቶች የዓለም ዋንጫ የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ ጅቡቲ እና ኤርትራ አዲስ አበባ ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡

የ2022 የዓለም ከ20 አመት በታች የሴቶች ዋንጫ በኮስታሪካ አስተናጋጅነት ይካሄዳል፡፡ ለዚህም ውድድር ይረዳ ዘንድ በአፍሪካ የሚገኙ ሀገራት የቅድመ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታቸውን ማድረግ የጀመሩ ሲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በቅርቡ በአንደኛ ዙር ማጣርያ ከሩዋንዳ አቻው ጋር የደርሶ መልስ መርሀግብሩን ያከናውናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህ የማጣሪያ ውድድር ላይ በምስራቅ አፍሪካ ዞን የሚገኘው የጅቡቲ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ከኤርትራ አቻው ጋር የፊታችን ዕሁድ ነሐሴ 9 በአዲስ አበባ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች፡፡ ጅቡቲ ላይ መደረግ የነበረበት የመጀመሪያው የማጣሪያ ጨዋታ መርሀግብር በሁለቱ ሀገራት መካከል ባለው ችግር ካፍ በገለልተኛ ሜዳ ሁለቱ ሀገራት ማድረግ አለባቸው በማለቱ ጨዋታው ኢትዮጵያ ላይ ሁለቱም የደርሶ መልስ ጨዋታዎች እንዲደረጉ ውሳኔን አስተላልፏል፡፡

ለዚህ ጨዋታ የኤርትራ ብሔራዊ ቡድን ወደ 28 የሚደርስ አባላት የያዘ የልዑካን ቡድንን በመያዝ በትላንትናው ዕለት አዲስ አበባ ሲገባ በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ተወካይ ሚካኤል እምሩ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ በአዝማን ሆቴል ማረፊያውን ያደረገ ሲሆን ልምምዱንም ከዛሬ ረፋድ ጀምሮ ማከናወን እንደሚጀምር ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡ በአንፃሩ የጅቡቲ ብሔራዊ ቡድን በዛሬው ዕለት አዲስ አበባ እንደሚገባ የሚጠበቅ ሲሆን ዕሁድ 10፡00 በአዲስ አበባው የአበበ ቢቂላ ስታዲየም መርሀግብራቸውን ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡