ዋልያው የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርግ ተገልጿል

ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከፊቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች የሚጠብቁት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የአቋም መፈተሻ ጨዋታ እንዳገኘ እየተነገረ ይገኛል።

በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከያዝነው ወር መጨረሻ ጀምሮ ላለበት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ዝግጅት ማድረግ መጀመሩ ይታወቃል። በአዳማ መቀመጫውን በማድረግ በቀን ሁለት ጊዜ ልምምዱን የሚሰራው ብሔራዊ ቡድኑም ከሁለት ሳምንታት በኋላ ከዩጋንዳ አቻው ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ እንደሚያደርግ የዩጋንዳ ብዙሃን መገናኛዎች እየዘገቡ ይገኛሉ።

በተለይ የዩጋንዳ እግርኳስ ፌዴሬሽን ይዞት በወጣው መረጃ መሠረት እንደ ዋልያው ሁሉ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ያሉበት የዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ወደ ጆርዳን አቅንቶ ዝግጅት ለማድረግ ለተጫዋቾች ጥሪ አቅርቧል። የቡድኑ አባላትም ነገ ከተሰባሰቡ በኋላ እዛው ሀገራቸው ከሦስት ቀን በኋላ ልምምድ ይጀምራሉ። ከዛም ቡድኑ ነሃሴ 15 ወደ ጆርዳን በማቅናት ሁለት የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን ከሶሪያ ጋር እንደሚያደርግ ተጠቁሟል።

በአሠልጣኝ ሰርጆቪች ሚሉቲን ሚቾ የሚመራው ቡድኑም ሁለቱን ጨዋታዎች ጆርዳን ላይ ካከናወነ በኋላ አብዛኛውን ከሀገር ውጪ የሚጫወቱ ተጫዋቾች በመያዝ ነሃሴ 21 ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጣ ታውቋል። በዚህም እሁድ ነሃሴ 23 ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን እንደሚያደርግ ተገልጿል።

ይህንን መረጃ በርካታ የዩጋንዳ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡት ቢገኝም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የአቋም መፈተሻ ጨዋታውን ለማድረግ ገና በንግግር ላይ እንደሚገኝ እና እስካሁን ማረጋገጫ እንዳልተሰጠው ለዝግጅት ክፍላችን ገልፆልናል። በተለይ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ንግግር ላይ እንዳሉም ተጠቁመናል።

ያጋሩ