በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ ተጋጣሚ የሆነችው ጋና በዛሬው ዕለት ስብስቧን ይፋ አድርጋለች።
በኳታር አስተናጋጅነት በሚካሄደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ውድድር ላይ ለመሳተፍ የአፍሪካ ሀገራት ከያዝነው ወር መጨረሻ ጀምሮ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። ለዚሁ ውድድር ለመብቃት በምድብ ሰባት ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባቡዌ ጋር የተደለደለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም የምድብ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከጋና አቻው ጋር የሚያደርግ ይሆናል። ለዚህ ወሳኝ የማጣሪያ ጨዋታ በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው ስብስብም ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ተሰባስቦ ከሦስት ቀናት በፊት ልምምድ ማድረግ ጀምሯል።
በአሠልጣኝ ቻርለስ አኮኖር የሚመሩት ጋናዎች ደግሞ ዛሬ ከሰዓት ከኢትዮጵያ እና ደቡብ አፍሪካ ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ ለ30 ተጫዋቾች ጥሪ ማቅረባቸው ታውቋል። ጥሪ ከቀረበላቸው ተጫዋቾች መካከል የአርሰናሉ ቶማስ ፓርቲ፣ የሌስተር ሲቲው ዳንኤል አማርቲ፣ የክሪስታል ፓላሱ ጆርዳን አይው እና የአልሳዱ አንድሬ አይው ተካተዋል።
የጋና ብሔራዊ ቡድንም ነሐሴ 28 ከኢትዮጵያ አቻው ጋር የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን የሚያደርግ ይሆናል።